ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን ያለ ባህር በር ዘግቶ መኖር የማይቻልና መቀጠል የሌለበት የህልውና ጉዳይ ነው

ሐረር፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን ያለ ባህር በር ዘግቶ መኖር የማይቻልና መቀጠል የሌለበት የህልውና ጉዳይ መሆኑን የቀድሞ የጦር አባላት ተናገሩ።

የባህር በር ከንግድና የምጣኔ ሃብት ፋይዳ ባሻገር ዓለም አቀፋዊ ትስስር፤ የጋራ ተጠቃሚነት፣ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮችና ሌሎች ጥቅሞችን ማረጋገጥ የሚቻልበት ወሳኝ መሰረተ ልማት መሆኑ ይታወቃል።

በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ ለዘመናት ይዞታዋ በነበረው የባህር በር ጥቅሟንና ክብሯን አስጠብቃ የኖረች ቢሆንም የዛሬ 30 ዓመት በውል ባልታወቀ ምክንያት ከባህር እንድትርቅ ተደርጓል።

የምጣኔ ሃብቷ በእድገትና ማንሰራራት ላይ የሚገኘውና በአፍሪካ ሁለተኛውን የህዝብ ቁጥር የያዘችው ኢትዮጵያን ከባህር የቅርብ እሩቅ አድርጎ መዝለቅ የማይቻልና የህልውና ጉዳይ ሆኗል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ የትውልድ ጥያቄ ሆኖ ለተግባራዊነቱ ጥረቱ ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑ ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(/) በቅርቡ በመከላከያ ሰራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65 ዓመት አከባበር ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ባህርን ለብሄራዊ ጥቅሟና ለቀጣናዊ ሰላምና ደህንነት ጭምር የመጠቀም ዓላማ ሰንቃ እየሰራች መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው በሐረር ከተማ የሚገኙ የቀድሞ ጦር አባላት፤ የኢትዮጵያ እና የባህር በር ተነጣጥሎ መኖር የሁላችንም ጥያቄና ቁጭት ሆኖ የቆየ ነው ብለዋል።

በመሆኑም አሁን ላይ የሀገር ህልውና እና የትውልድ ጥያቄ ሆኖ መምጣቱ ተገቢ መሆኑን አንስተው ለምላሹ የሁላችንም ጥረት ያስፈልጋል ነው ያሉት


 

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል መቶ አለቃ ውቤ ታሪኩ፤ ኢትዮጵያ ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ሁኔታ ከባህር እንድትርቅ መደረጉ ትልቅ የታሪክ ስብራት መሆኑን አንስተው ወደ ባህር የምትመለስበት ጊዜ እሩቅ እንደማይሆንም ተናግረዋል

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን ከራሷ ብሄራዊ ጥቅም ባለፈ ለቀጣናዊ ትስስር፣ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በልማት እየበለጸገችና ኢኮኖሚዋን የሚያሳልጥ የገቢና ወጪ ንግድ ስራዎች እያደገ እንደሚገኝ ጠቁመው ይህን ኢኮኖሚ መሸከም የሚችል የባህር በር ይገባናልና ማስመለስ አለብን ነው ያሉት

ኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤት ለማድረግ ትውልዱ የጀመረውን ጥረት አድንቀው የተጀመረው ጥረት ከግብ እንዲደርስ የሁላችንም አደራ ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል


 

ሌላኛው የቀድሞ የጦር አባል ሃምሳ አለቃ በፍቃዱ ፈይሳ፤ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ደማቸውን የገበሩበት የባህር በር በሴራ ፖለቲካ እንድታጣ የተደረገበት መንገድ የዘመናት ቁጭት መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት የሀገሪቱን ልማትና ሰላም እያጎለበተና የህዝቡን ተጠቃሚነት እያሳደገ ይገኛል ለዚህም ታላላቅ የሀገራት መሪዎች ምስክርነታቸውን እየሰጡ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም በታሪክ፣ በመልክአ ምድርና በህግ አግባብ የኢትዮጵያ አካል የነበረው የባህር በር የሚመለስበት ጊዜ እሩቅ መሆን የለበትም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም