በወለጋ ዞኖች የተጀመሩ የልማት ስራዎች የህዝቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ እና የአካባቢውን እምቅ አቅም ለመጠቀም የሚያስችሉ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በወለጋ ዞኖች የተጀመሩ የልማት ስራዎች የህዝቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ እና የአካባቢውን እምቅ አቅም ለመጠቀም የሚያስችሉ ናቸው
ነቀምቴ፣ የካቲት 26/2018 (ኢዜአ)፦ በወለጋ ዞኖች የተጀመሩ የልማት ስራዎች የህዝቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ እና የአካባቢውን እምቅ አቅም ለመጠቀም የሚያስችሉ ናቸው ሲሉ በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ መምህራን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በቄለም ወለጋ፣ በምስራቅ ወለጋ እና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን መጎብኘታቸው ይታወሳል።
በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአካባቢው አመርቂ እድገት እና ለውጥን የሚያሳዩ ዐበይት የልማት ሥራዎችን መመልከት መቻላቸውን ገልጸው በተለይም የግብርና፣ የማዕድን እና የኮሪደር ልማት ስራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን አንስተዋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህራን ጋር ቆይታ ያደረገ ሲሆን መምህራኑም በዞኖቹ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ለሁለንተናዊ እድገት መሰረትን የሚጥሉ ናቸው ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተባባሪ ፕሮፌሰር ገመቹ ሙላቱ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በአካባቢው ባለፉት ዓመታት አጋጥሞ የነበረው የጸጥታ ችግር መቀረፉ ለልማት ስራዎች ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
በአካባቢው የተገኘው ሰላም የመንገድ፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የኃይል፣ የንጹህ ውሃና የቴሌኮም መሠረተ ልማት እንዲስፋፉ አድርጓል ብለዋል።
ይህም የአካባቢውን እምቅ የልማት አቅም ጥቅም ላይ እንዲውል ከማስቻሉም በላይ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ መሰረት ይጥላል ነው ያሉት።
እነዚህ ስራዎች የገበያ ትስስርን ከማጠናከር ባለፈ ለቀጣዩ ትውልድ ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ጠቅሰው ለፕሮጀክቶቹ ውጤታማነት በጋራ መቆም እንደሚገባ አስረድተዋል።
ዩኒቨርሲቲውም በምርምርና በቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድ የአካባቢውን ልማት የሚያፋጥኑ ስራዎች ላይ አተኩሮ በመስራት ድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላኛው በዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚክስ መምህር እሱባለው ዳባ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መንግስት ህብረተሰቡን በማስተባበር እያከናወነ የሚገኘው ስራ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
በወለጋ ዞኖች የተገኘውን ሰላም በመጠቀም ሀብትን ወደ ልማት በመቀየር ረገድ የተጀመረው ስራ ከአካባቢው አልፎ ለአገርም ተስፋ መሆኑን አብራርተዋል።
በተለይም በከተሞች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ የከተሞችን ገጽታ በመቀየር ለኢንቨስትመንት ሳቢ ማድረጉን ጠቅሰው የህዝቡን ጤና ለመጠበቅ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም አምራች አርሶ አደሮች ምርታቸውን በቀጥታ ለማዕከላዊ ገበያ እንዲያቀርቡና ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኙ በር መክፈቱን ገልጸዋል።
በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው የታዩ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠልና ጉድለቶችን በህዝብ ተሳትፎ በመሙላት፣ የልማት ስራዎቹን ይበልጥ ውጤታማ የማድረግ ሚናውን ያጠናክራል ብለዋል።