ቀጥታ፡

በባሌ ሮቤ የተጀመረው የፓስፖርት አገልግሎት የተገልጋዮችን እንግልትና ወጪ መቀነስ አስችሏል

ሮቤ፣ የካቲት 26/2018 (ኢዜአ)፦ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በባሌ ሮቤ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከፍቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይደርስባቸው የነበረውን እንግልትና ወጪ ማስቀረቱን ተገልጋዮች ገለጹ።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋፋት ባከናወናቸው የሪፎርም ሥራዎች፣ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተጨማሪ ቅርንጫፎችን መክፈቱ ይታወሳል።


 

በቅርቡ በባሌ ሮቤ የተከፈተው ቅርንጫፍም የዚሁ ጥረት አካል ሲሆን ኢዜአ ያነጋገራቸው ተገልጋዮች እንደገለጹት፤ ተቋሙ አገልግሎቱን ወደ አቅራቢያቸው ማምጣቱና አሰራሩን ማዘመኑ ቀደም ሲል የነበረውን አድካሚ ሂደት አስቀርቷል።

የአጋርፋ ወረዳ ነዋሪዋ ሰሚራ አብዱሪ "ቀደም ሲል የፓስፖርት አገልግሎት ለማግኘት ወደ አዳማ፣ ሐዋሳና አዲስ አበባ በመጓዝ ቀናትን የሚወስድ ምልልስ ማድረግ ይጠበቅብን ነበር'' ብለዋል። 


 

አሁን ግን በኦንላይን የጀመሩትን ሂደት በቀጠሯቸው መሰረት ፓስፖርት ለመረከብ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

የሮቤ ከተማ ነዋሪዋ ሰአዳ ሁሴን  ፓስፖርት ለማውጣትና ለማደስ ወደ ሌላ ሩቅ አካባቢ መሄድ ግዴታ በመሆኑ ተገልጋዩ ከፍተኛ ምሬት ውስጥ እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን አገልግሎቱ በአቅራቢያቸው መጀመሩ ትልቅ እፎይታ መሆኑን ተናግረዋል።

የሮቤ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጀማል አባገሮ በበኩላቸው፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በከተማዋ ቅርንጫፍ መክፈቱ ህዝቡ ሲያነሳው የቆየውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የመለሰ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

ለሥራው ስኬታማነት አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በባሌ ሮቤ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ አዲስአለም ንጉሴ እንደገለጹት፤ ቅርንጫፉ የሮቤና የባሌ ዞን ነዋሪዎችን በቅርበት ለማገልገል ያስችላል።


 

አክለውም ተገልጋዮች በኦንላይን መረጃቸውን አጠናቅቀው በተሰጣቸው ቀጠሮ ብቻ ወደ ቅርንጫፉ በመምጣት አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ ገልጸዋል።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ባከናወናቸው የሪፎርም ሥራዎች፣ ዘመናዊና ቀልጣፋ አሰራርን እየገነባ መሆኑን ተቋሙ በተለያዩ ጊዜያት መግለጹ ይታወሳል።
 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም