ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ሀዲያ ሆሳዕና ከአዳማ ከተማ በሃዋሳ  ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ሀዲያ ሆሳዕና በሊጉ እስከ አሁን ሰባት ጨዋታዎችን አሸንፏል። ስምንት ጊዜ ሲሸነፍ ስድስት ጊዜ አቻ ተለያይቷል። በ21ቱ ጨዋታዎች ላይ 18 ግቦችን ሲያስቆጥር 21 ጎሎች ተቆጥረውበታል። 

ቡድኑ በ27 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል። 

በሊጉ ካከናወናቸው 21 ጨዋታዎች መካከል ሰባቱን ያሸነፈው አዳማ ከተማ በበኩሉ ሶስት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ 11 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 19 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 17 ጎሎችን አስተናግዷል።

አዳማ ከተማ በ32 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል። 

ጨዋታው ሀዲያ ሆሳዕና ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ፣ በ21ኛ ሳምንት ከሸገር ከተማ ጋር ሶስት አቻ የተለያየው አዳማ ከተማ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ የሚያደርጉት ነው። 

በሌላኛው መርሐ-ግብር መቀሌ 70 እንደርታ ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

መቀሌ 70 እንደርታ በሊጉ ካደረጋቸው 21 ጨዋታዎች መካከል በአራቱ አሸንፎ በሰባቱ ተሸንፎ 10 ጊዜ አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 14 ግቦችን ሲያስቆጥር 22 ጎሎችን አስተናግዷል።

ቡድኑ በ22 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ እስከ አሁን በሊጉ 21 ጨዋታዎችን አድርጎ አምስት ጊዜ ሲያሸንፍ በስድስቱ ተሸንፏል። በቀሪ 10 ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። 14 ግቦችን ሲያስቆጥር 21 ጎሎችን አስተናግዷል። 

ድሬዳዋ ከተማ በ25 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዟል። 

በ21ኛ ሳምንት መቀሌ 70 እንደርታ ከመቻል ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል። ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ ባለፉት ሶስት የሊጉ ጨዋታዎች አላሸነፈም።

ሁለቱ ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም