ቀጥታ፡

የውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው እና የመውረድ ስጋት ያንዣበበት ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከክሪስታል ፓላስ ጋር ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2018 (ኢዜአ)፦ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 29ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል።

በዕለቱ ብቸኛ መርሐ-ግብር ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከክሪስታል ፓላስ በቶተንሃም ሆትስፐርስ ስታዲዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ቶተንሃም ሆትስፐርስ በ29 16ኛ ደረጃን ይዟል። ክሪስታል ፓላስ በ35 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዟል።

ባለፉት 10 የሊግ ጨዋታዎች ድል የናፈቀው ቶተንሃም በውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ ይገኛል።

የሰሜን ለንደኑ ክለብ ቶማስ ፍራንክን አሰናብቶ ኢጎር ቱዶርን በአሰልጠጣኝነት ቢቀጥርም ውጤቱ ላይ የተሻለ ነገር ማምጣት አልቻለም።

ኢጎር ቱዶር እስከ አሁን ቡድናቸውን እየመሩ ባደረጉት ሁለት የሊግ ጨዋታ በአርሰናል 4 ለ 1 እና በፉልሃም 2 ለ 1 ተሸንፈዋል።

አዲሱ አሰልጣኝ የውጤት ማጣት ቀውሱን በመቀልበስ ቡድኑን ከመውረድ ለመታደግ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ግድ ይላቸዋል።

ቶተንሃም ሆትስፐርስ ለመጨረሻ ጊዜ በሊጉ ያሸነፈው የዛሬው ተጋጣሚውን ክሪስታል ፓላስን ነው።

ቡድኖቹ በ18ኛ ሳምንት ባደረጉት ጨዋታ ቶተንሃም ሆትስፐርስ በአርቺ ግሬይ ጎል 1 ለ 0 አሸንፏል።

የደቡብ ለንደኑ ክሪስታል ፓላስ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ወጥ አቋም ማሳየት ተስኖታል።

ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው ሁለት ብቻ ነው።

በ28ኛ ሳምንት በማንችስተር ዩናይትድ የ2 ለ 1 ሽንፈት ያስተናገደው ክሪስታል ፓላስ ወደ ድል ለመመለስ ይጫወታል።

የ42 ዓመቱ አንድሪው ማድሊ የለንደን ክለቦቹን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም