የመንግሥታቱ ድርጅትና ዓለምአቀፍ የገንዘብ ተቋማት የአፍሪካን ፍትሐዊ ውክልና የሚያረጋግጥ የሪፎርም እርምጃዎች ሊተገብሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የመንግሥታቱ ድርጅትና ዓለምአቀፍ የገንዘብ ተቋማት የአፍሪካን ፍትሐዊ ውክልና የሚያረጋግጥ የሪፎርም እርምጃዎች ሊተገብሩ ይገባል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2018(ኢዜአ)፦ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤትና ዓለምአቀፍ የገንዘብ ተቋማት የአፍሪካን ፍትሐዊ ውክልና የሚያረጋግጥ የሪፎርም እርምጃዎች ሊተገብሩ እንደሚገባ ተገለጸ።
የአማኒ አፍሪካ ሚዲያ ጥናትና ምርምር ተቋም ከጃፓን ኤምባሲ ጋር በመሆን የተባበሩት መንግሥታት ሪፎርም ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ አካሂዷል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤትና ዓለምአቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ ቢሆኑም በተቋማዊ አወቃቀር ሥርዓት ላይ አፍሪካን ፍትሐዊ ውክልና ያገለሉ ናቸው።
የአማኒ አፍሪካ ዳይሬክተር ሰለሞን አየለ ደርሶ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የመንግስታቱ ድርጅት መዋቅር የአፍሪካን ፍትሐዊ ውክልና የሚያረጋግጥ የሪፎርም እርምጃ ሊወስድ ይገባል።
በተቋማቱ የአፍሪካን ፍትሐዊ ውክልና ለማረጋገጥም ግንዛቤን የሚያስጨብጥ ተከታታይ ሥራ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።
የአህጉሪቱ አባል ሀገራትና ከሌሎች ሀገራት ጋር ትብብርን በማጠናከር የአፍሪካን የዓለምአቀፍ ተቋማት ፍትሐዊ ውክልና ማስከበር የሚስችል መዋቅራዊ የሪፎርም እርምጃ እንዲወሰድ መስራት ይገባል ብለዋል።
የአማኒ አፍሪካ ሚዲያ ጥናትና ምርምር ተቋም የአፍሪካን ፍትሐዊ ውክልና ለማረጋገጥ በአፍሪካ ሕብረትና የአፍሪካ ዳያስፖራ ጉዳዮች ላይ በጥናትና ምርምር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የጋና አምባሳደር ሮበርት አፍሪይ(ዶ/ር)፤ አፍሪካ ለዓለም አቀፍ ተቋማት ያቀረበችው ፍትሐዊ የውክልና ጥያቄ ችላ በመባሉ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ የሌላት ብቸኛ አህጉር አድርጓታል ብለዋል።
ለዚህም የመንግስታቱ ድርጅት አፍሪካ በተሸከመችው የጸጥታው ምክር ቤት የሥራ ጫና ልክ ውክልና የሚያስገኛትን የሪፎርም እምርጃ መውሰድ እንዳለበት ገልጸዋል።
በአፍሪካ ሕብረት የጃፓን ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ኖቦሩ ሴኪጉቺ በበኩላቸው፤ አፍሪካ በመንግስታቱ የጸጥታው ምክር ቤትና በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ላይ ፍትሐዊ ውክልና ሊሰጣት ይገባል ብለዋል።
ጃፓንም አፍሪካ በመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤትና በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የሚኖራትን ፍትሐዊ ውክልና ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት ድጋፏን እንደምታጠናክር አረጋግጠዋል።
ጃፓንና የጂ-4 አባል ሀገራት የአፍሪካን ዓለም አቀፍ ፍትሐዊ ውክልና ለማረጋገጥ ሙሉ ድጋፍ እንደሚሰጡም አስታውቀዋል።
በተለይም እ.ኤ.አ. በ2024 በጸደቀው "የወደፊት ስምምነት" ላይ የጸጥታው ምክር ቤት መዋቅራዊ የማሻሻያ እርምጃ ለመወሰድ የተቀመጠው አቅጣጫ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቅሰዋል።