ለምርጫ ስኬታማነት የዜጎች ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለምርጫ ስኬታማነት የዜጎች ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2018(ኢዜአ)፡- ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት የዜጎች ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ገለፁ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለጠቅላላ ምርጫው ያዘጋጀው "ምርጫች ነው - ሀገር ያለእኛ" ህብሬ ዜማ ማስመረቂያ መርኃ ግብር ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ምርጫው ስኬታማ የሚሆነው ዜጎች በንቃት ሲሳተፉ፣ ሲመዘገቡ እና ድምፃቸውን ሲሰጡ ነው ።
በዚህም በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች ያላቸውን ተሳትፎ ለማነቃቃት፣ ለማበረታታት እና ለመቀስቀስ የመራጮች ትምህርት ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ ነው ብለዋል።
በዛሬው ዕለት የተመረቀው ህብረ ዜማ ዜጎች በምርጫው ሂደት ያላቸውን ባለቤትነት እንዲረዱ እና ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ ለማነቃቃት፣ ለማበረታታት እና ለማነሳሳት የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
የጥበብ ሥራዎች ዜጎችን የማስተማር እና የማነቃቃት ትልቅ አቅም እንዳላቸው በመጥቀስ፤ ይህ የህብሬ ዜማም መልዕክቱ በቀላሉ ወደ ህዝቡ እንዲደርስ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
ቦርዱ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ገለልተኛ እና አካታች ለማድረግ የጀመረውን ዝግጅት አጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል ።
በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የመራጮች ምዝገባ የፊታችን ቅዳሜ ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ይካሄዳል።