ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም አትሌቲክስ ውድድርን ልታዘጋጅ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የዓለም አትሌቲክስ ውድድርን ለመጀመሪያ ጊዜ ለማስተናገድ እድል ማግኘቷን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ። 


 

በዚህም መሠረት ውድድሩ ሚያዝያ 10 ቀን 2018 ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኘው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ይካሄዳል። 

የዓለም አትሌቲክስ የውድድር ዋና ዳይሬክተር ፒርስ ኦክላጋን በየካቲት ወር መጀመሪያ በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

የዓለም አትሌቲክስ የውድድር ዋና ዳይሬክተር ፒርስ ኦክላጋን የአትሌቲክስ መሰረተ ልማቶችን ጎበኙ


 

በዚሁ ወቅትም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማዘጋጀት በቂ ዐቅም እንዳላት ገልጸው፤ የተለያዩ  ውድድሮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ እናደርጋለን ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ይህ ተከትሎም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር በዓለም አትሌቲክስ ዓመታዊ መርሐ-ግብር ዛሬ ተካትቷል።

ውድድሩን የዓለም አትሌቲክስ ከፍተኛ ባለሙያዎች የሚመሩት በመሆኑ፤ ለኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ሙያተኞች ልምድ ለማግኘት የሚያስችል ነው ተብሏል።


 

ውድድሩ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ አትሌቶች የሚሳተፉበት ከመሆኑ ባሻገር አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች ከፍተኛ ሽልማት እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም