ተዓማኒነት ያላቸውን መረጃዎች በማጋራት የኢትዮጵያን የብሔራዊ ደኅንነት አጀንዳዎች ማሳካት ከዜጎች ይጠበቃል - ኢዜአ አማርኛ
ተዓማኒነት ያላቸውን መረጃዎች በማጋራት የኢትዮጵያን የብሔራዊ ደኅንነት አጀንዳዎች ማሳካት ከዜጎች ይጠበቃል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2018 (ኢዜአ)፡- ዜጎች ተዓማኒነት ያላቸውና ተጨባጭ መረጃዎችን በማጋራት የኢትዮጵያን የብሔራዊ ደኅንነት አጀንዳዎች ለማሳካት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጠየቀ።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከኅብረተሰቡ መረጃ የሚቀበልበትና ሌሎችም የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጥ የኮሙኒኬሽን ፕላትፎርም ይፋ አድርጓል።
አገልግሎቱ ለኢዜአ በላከው መረጃ እንዳመለከተው፤ በተቋሙ የውስጥ ዐቅም የበለፀገው ከመደበኛው ድረ-ገጽ በብዙ ገፅታዎቹ የሚለየው የኮሙኒኬሽን ፕላትፎርም ዜጎች በፀጥታ፣ በደኅንነትና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ከየትኛውም ስፍራ ሆነው መረጃ የሚሰጡበት የሪፖርት ማድረጊያ ክፍል አለው፡፡
ሀገራዊ የደኅንነት፣ የመረጃና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተም ወቅታዊ መረጃዎችን ያጋራል ነው የተባለው።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እንዳሉት፤ የኮሙኒኬሽን ፕላትፎርሙ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚያጋጥም የስጋት ተጋላጭነትን የተመለከቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎች የሚሰጥ ነው።
ኅብረተሰቡም ሆነ የውጭ ዜጎች መረጃውን በመጠቀም በየትኛውም ስፍራ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በማገዝ ከፍተኛ ሚና ያበረክታል ነው ያሉት።
የኮሙኒኬሽን ፕላትፎርሙ ለወደፊቱ የተቋሙን መስፈርት የሚያሟሉና ልዩ ተሰጥዖ ያላቸው ዜጎች አገልግሎት መሥሪያ ቤቱን በመቀላቀል ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ የሚያስችል የማመልከቻ ገጽ የተካተተበት መሆኑንም አስታውቀዋል።
ፕላትፎርሙ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ እያከናወነ በሚገኘው ሪፎርም ሀገር በቀል ቴክኖሎጂ በማበልፀግ የላቀ የመፈፀም ዐቅም ያለው ተቋም ለመገንባት የሚደረገው ጥረት አካል መሆኑም ተጠቁሟል።
ዜጎችም ተዓማኒነት ያላቸውና ተጨባጭ መረጃዎችን በማጋራት የኢትዮጵያን የብሔራዊ ደኅንነት አጀንዳዎች ለማሳካት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ተጠይቀዋል።
የኮሙኒኬሽን ፕላትፎርሙ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የደኅንነት ተጋላጭነት ፍተሻ ተደርጎለት የማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንደተሰጠው ተመላክቷል።