የአፈጣጠር ችግር ያለባቸው ህጻናት ምቹና ተደራሽ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአፈጣጠር ችግር ያለባቸው ህጻናት ምቹና ተደራሽ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ጎንደር፤ የካቲት 25/2018 (ኢዜአ) ፡-በኢትዮጵያ የአፈጣጠር ችግር ያለባቸው ህጻናት ምቹና ተደራሽ የጤና አገልግሎት የሚያገኙበትን የህክምና ስርአት ለመዘርጋት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የጎንደር ዩንቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአፈጣጠር ችግር ላለባቸው ህጻናት ያቋቋመው የኒውሮሰርጀሪና የፊዚዮቴራፒ ህክምና አገልግሎት መስጫና ማገገሚያ ማእከል ተመርቆ ተከፍቷል፡፡
በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ በሚኒስቴሩ የስፔሻሊቲና ተሃድሶ ዴስክ ሃላፊ ዶክተር ኤርሚያስ ሙላቱ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ የአፈጣጠር ችግር ያለባቸው ህጸናት በቂ የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት አንድ ወጥ ስርአት ባለመዘርጋቱ ህጸናቱን ተደራሽ የሚያደርግ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ውስንነቶች አሉ።
አገልግሎቱን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ እንዲቻል የህክምና ባለሙያዎችን አቅም ከማጎልበት ጀምሮ ለህክምና አሰጣጡ አጋዥ የሆኑ መድሃኒቶችንና የህክምና መሳሪያዎችን በማሟላት ረገድ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በህጻናት የአፈጣጠር ችግር ከሚስተዋሉ የጤና እክሎች መካከልም የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ፣ የነርቭ ዘንግ ክፍተት፣ የአጥንትና ጡንቻ መላላትና የአእምሮ እድገት ውስንነት ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ያቋቋመው ማእከል የአፈጣጠር ችግር ያለባቸው ህጻናት የተሟላ ህክምና አግኘተው ጤናማና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ የሚያግዝ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
በምክትል ፕሬዝዳንት ማእረግ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ጌታው ብርሃን የማእከሉ መቋቋም የአፈጣጠር ችግር ያለባቸው ህጻናት አገልግሎቱን በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል ።
ማእከሉ አገልግሎቱን በጥራት ለመስጠት መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡
ማእከሉ የአፈጣጠር ችግር ላለባቸው ህጻናት የቀዶ ህክምናን ጨምሮ በረጅም ጊዜ ሂደት አገግመው ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ በማድረግ በኩል አካላዊና ስነ ልቦናዊ ድጋፎችን እንደሚያደርግ የገለጹት ደግሞ የማእከሉ አስተባባሪ ረዳት ፕሮፌሰር ኢሳያስ አደፍርስ ናቸው፡፡
ሪች አናዘር ፋውንዴሽን የተባለ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅትም ግምታቸው ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የአካል ድጋፍ ቁሳቁሶችንና ዘመናዊ የአልትራሳውንድ የህክምና መሳሪያዎችን ለማእከሉ መለገሱንም ተናግረዋል፡፡
የአፈጣጠር ችግር የህክምና አገልግሎት ሳምንት ንቅናቄ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተካሄደ መሆኑ ተመልክቷል፡፡