ቀጥታ፡

በክልሉ ኮሌጆች ከስልጠና በተጨማሪ ለቴክኖሎጂና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል

ወላይታ ሶዶ፤ የካቲት 25/2018 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች  ለቴክኖሎጂና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ተገለጸ።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሶዶ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የሥራ እንቅስቃሴን ዛሬ ተመልክተዋል። 


 

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ የሚገኙ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች እንዲሁም ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ከስልጠና ሥራቸው በተጨማሪ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና በሥራ ዕድል ፈጠራ ዜጎችን ተጠቃሚ ሊያደርጉ ይገባል፡፡

በተለይ በኮሌጆቹ የሚሰጡ ስልጠናዎች የህዝብን ችግር የሚፈቱ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችሉ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። 

ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን ከማፍራት ባለፈ ስልጠናውን ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በማቀናጀት የዜጎችን በተለይ የወጣቱን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። 

በዚህም ተቋማቱ የውስጥ ገቢያቸውን በማጎልበት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ኮሌጆቹ ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን ማፍራት እንዳለባቸው ያሳሰቡት አበባየሁ (ዶ/ር)፣ ውጤታማ የስልጠናና የፈጠራ ሥራዎችን እንዲያከናውኑም  የክልሉ መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል ያጠናክራል ብለዋል።

የዛሬው የመስክ ምልከታም በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለይቶ ለመፍታትና ጠንካራ ጎኖችን ለማስቀጠል ያለመ መሆኑን ነው የገለጹት።


 

የሶዶ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን ኢንጂነር ያዕቆብ ያሲን በበኩላቸው ኮሌጁ በአውቶሞቲቭ፣ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ እንዲሁም በሌሎች የሙያ መስኮች ብቁ ዜጎችን ለማፍራት እየሰራ ይገኛል።

ኮሌጁን የዲጂታል ማዕከል ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፣ ለዚህም በአሁኑ ወቅት ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የዳታ ማዕከል ተገንብቶ ለአገልግሎት በቅቷል ብለዋል።

ኮሌጁ በአሁኑ ወቅት 1ሺህ 944 ሰልጣኞችን ተቀብሎ እያሰለጠነ ሲሆን የስልጠና ሂደቱም ከሀገር ውስጥ ባለፈ በውጭ አገር የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለመሆን እያገዘ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመስክ ምልከታው ላይ የክልሉ፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም