ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2018(ኢዜአ)፦ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ50ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8) አስመልክቶ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሴቶችን እኩልነትና መብቶች ለማስከበር በርካታ መስዋዕትነት ያስከፈሉ ትግሎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
የዚህ ትግል ውጤትም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እውቅና በማግኘት የሴቶችን መብት የሚያስከብሩ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች እንዲወጡ ፋና ወጊ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ በሰጠው ልዩ ትኩረት በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ተጨባጭ ለውጦች መታየታቸውን ጠቁመዋል።
በፖለቲካዊ ውሳኔ ሰጪነት ረገድ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ውክልና 41 በመቶ መድረሱን ጠቅሰው በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሴቶች ተሳትፎ 50 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል፡፡
የዘንድሮው የሴቶች ቀን አከባበር ባለፉት 50 ዓመታት የተከናወኑ ስራዎችንና የተገኙ ውጤቶችን ከመገምገም ባለፈ በቀጣይ የሚቀሩ የቤት ስራዎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
በዓሉን በማስመልከት ህብረተሰቡን ያሳተፉ ሰፋፊ ንቅናቄዎች የሚከናወኑ ሲሆን ኤግዚቢሽንና ባዛሮች፣ የጡት ካንሰር ምርመራ፣ የማህፀን በር ካንሰር ምርመራና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እንደሚከናወኑም ጠቁመዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ50ኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን “50ኛው ዓመት የሴቶች ድምፅ ለእኩልነትና ለበለፀገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሐሳብ ይከበራል።