በተጠባቂው ጨዋታ ሲዳማ ቡና ፋሲል ከነማን በማሸነፍ መሪነቱን አጠናከረ - ኢዜአ አማርኛ
በተጠባቂው ጨዋታ ሲዳማ ቡና ፋሲል ከነማን በማሸነፍ መሪነቱን አጠናከረ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ሲዳማ ቡና ፋሲል ከነማን 1 ለ 0 አሸንፏል።
በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ካሜሮናዊው አጥቂ ብለሥ ናጎ በ92ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል።
ሲዳማ ቡና ነጥቡን ወደ 42 ከፍ በማድረግ መሪነቱን አጠናክሯል። ከተከታዩ ነገሌ አርሲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነትም ወደ አምስት ከፍ አድርጓል።
በውድድር ዓመቱ 11ኛ ድሉንም አስመዝግቧል።
በአንጻሩ በሊጉ አምስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ፋሲል ከነማ በ33 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አላሸነፈም።
በሌላኛው መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ቡና ባህርዳር ከተማን 2 ለ 0 አሸንፏል።
በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ቢኒያም ጌታቸው እና ዘላለም አባተ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
በሊጉ ተከታታይ ድሉን ያስመዘገበው ኢትዮጵያ ቡና አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ29 ነጥብ ደረጃውን ከ11ኛ ወደ 7ኛ ከፍ አድርጓል። በውድድር ዓመቱም ስምንተኛ ድሉን አስመዝግቧል።
በውድድር ዓመቱ አምስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ባህርዳር ከተማ በ27 ነጥብ ከነበረበት ስምንተኛ ደረጃ ወደ ዘጠነኛ ዝቅ ብሏል።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ አርባምንጭ ከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም፣ ወላይታ ድቻ ከሃዋሳ ከተማ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።