ቀጥታ፡

ሚኒስቴሩ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቁ የሰው ኃይል ለማቅረብ ይሰራል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2018(ኢዜአ)፦ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛና በሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢኒስቲትዩት ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቁ የሰው ሃይል ለማቅረብ እንደሚሰራ ተገለጸ።

የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ጋር በሰው ሃይል አቅርቦት እና ስልጠና ዘርፎች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ(ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የሰው ሀብት አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ በቀለ ባይ ተፈራርመውታል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በሰው ሃይል አቅርቦት፣ ስልጠና ዘርፎች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸው ነው።

ሚኒስቴሩ በስሩ ባሉ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ፣ በሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢኒስቲትዩት እንዲሁም ሌሎች ተጠሪ ተቋማት በኩል ለአየር መንገዱ ብቁ የሰው ሃይል ለማቅረብ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ለዚህም ስምምነቱን ወደ ስራ ለማስገባት ዝርዝር ዕቅዶች ተዘጋጅቶ የሁለቱ ተቋማት የስትሪንግና ቴክኒክ ኮሚቴ በጋራ ርብርብ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአቪዬሽን ዘርፍ ይበልጥ ተወዳዳሪ እንዲሆን በማድረግ በኩል ስምምነቱ አወንታዊ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የሰው ሀብት አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ በቀለ ባይ በበኩላቸው፤ አየር መንገዱ በየአመቱ በአማካይ ከ3500 እስከ 4000 ሰዎችን በቅጥር እንደሚቀበል ተናግረዋል።

አየር መንገዱ ከስራና ክህሎት ጋር በጋራ መስራቱ የቅጥር ሂደቱን ውጤታማ ከማድረግ ባለፈ የስራ ድግግሞሽን የሚያስቀር ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም