ሀገራዊ ለውጡ የሴቶች የፖለቲካ ውክልናና የውሳኔ ሰጪነት አቅምን በተግባር አረጋግጧል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ለውጡ የሴቶች የፖለቲካ ውክልናና የውሳኔ ሰጪነት አቅምን በተግባር አረጋግጧል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2018(ኢዜአ)፦ሀገራዊ ለውጡ የሴቶች የፖለቲካ ውክልናና የውሳኔ ሰጪነት አቅምን በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን የሴቶች አደረጃጀቶች ገለፁ።
በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የሴቶች ክንፍ ኃላፊ ሳሚያ አብደላ እንዳሉት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በኦሮሚያ ክልል ለሴቶች ልዩ ትኩረት በመሰጠቱ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በክልሉ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎና የውሳኔ ሰጪነት ሚና በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን ጠቁመው፣ ይህም ለለውጡ ስኬት ትልቅ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
የሴቶች በኢኮኖሚው ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ያነሱት ወይዘሮ ሳሚያ ይህም ምርታማነታቸውን በማሳደግ ረገድ የጎላ ድርሻ እንዳለውና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጠ መሆኑን አስረድተዋል።
በትምህርት፣ በጤናና በሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ስኬታማ ተግባራትን ይበልጥ ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የዲሞክራሲ ግንባታ ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የሴቶች ክንፍ ፅህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ብሩክ ባልቻ በበኩላቸው ሴቶች ለኢትዮጵያ ብልፅግና መረጋገጥ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ልማትን ለማረጋገጥ የሴቶች ድርሻ ጉልህ እንደሆነ ጠቁመው ሴቶች በፖለቲካ ያላቸው ተሳትፎ እያደገ በመምጣቱ ለሀገር አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ እያደገ መሆኑን የገለፁት ደግሞ በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የሴቶች ክንፍ ፅህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ፀደኒያ ግርማይ ናቸው።
የለውጡ ዓመታት የሴቶች የውሳኔ ሰጪነት በተግባር እየተረጋገጠ የመጣበት እንደሆነም ነው ያስረዱት።
የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ ምክትል ፕሬዝዳንት መስከረም አበበ በበኩላቸው ሴቶች ህብረ ብሄራዊ ሀገር ለመገንባትና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ በተግባር የሚያረጋግጡ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀው በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ ከሴቶች አደረጃጀትና ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለአንድ ወር ያህል የዘለቀ ሀገራዊ የንቅናቄ መድረክ 10 ሚሊየን በላይ ሴቶችን ማወያየት መቻሉን ጠቅሰዋል።