በባህርዳር ከተማ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በባህርዳር ከተማ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል
ባህርዳር፤ የካቲት 25/2018 (ኢዜአ)፡-በባህርዳር ከተማ ሰላምን በማፅናት የተጀመሩ ውጤታማ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ገለፁ።
የባህርዳር ከተማ አስተዳደር "ለሰላም ዘብ ዕንቆማለን፤ የልማት አርበኛ እንሆናለን" በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጀው የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።
ምክትል ከንቲባው አቶ አስሜ ብርሌ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ አመራሩ፣ የፀጥታ ኃይሉና ሕዝቡ በቅንጅት ያከናወኑዋቸው ተግባራት ውጤታማ ናቸው።
በኮሪደር ልማት፣ በመንገድ፣ በስማርት ሲቲ ግንባታ፣ በመሶብ አንድ ማዕከል የአገልግሎት መስጫና ዲጂታላይዜሽን ትግበራ ላይ የተከናወኑት ተግባራት ከተማዋን ከማዘመን ባለፈ ማሕበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ አስችለዋል ነው ያሉት።
እየተከናወኑ የሚገኙ የሰላም፣ የልማትና ለመልካም አስተዳደር ተግባራትን ቀጣይነት እንዲኖራቸው ለማድረግም ከማሕበረሰቡ ጋር በቅንጅት የሚከናወኑ ስራዎች ትኩረት እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል።
በተለይም በመጭው ግንቦት ወር 2018 ዓ.ም የሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን አጠናክሮ መሔድ ያስፈልጋል ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የህዝብ ግንኙነት አማካሪ አቶ ሞላ ሁሴን በበኩላቸው፤ አመራሩ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በቅንጅት በመስራቱ የከተማው ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ እንዲገኝ ማድረጉን አስረድተዋል።
ይህም የከተማዋን ገፅታ በመሰረታዊነት ከመቀየር ባሻገር ማሕበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሁሉን አቀፍ የልማት ተግባራት ለማከናወን ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ነው ያመለከቱት።
''ከግጭት የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ መረዳት ይገባል'' ያሉት የመድረኩ ተሳታፊ አቶ ዘውዱ ዘለቀ በተለይም ወጣቱ ወደ ሰላም በመምጣት ተግቶ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።
በከተማዋ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት የከተማዋ ገፅታ ከመቀየር ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል።
በንቅናቄ መድረኩም የአስተዳደሩ፣ የክፍለ ከተማና የቀበሌ አመራሮች ተሳትፈዋል።