ቀጥታ፡

በቦሌ በሻሌ ኮንዶሚኒየም የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረትን መቅረፍ ያስቻለ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ተከናወነ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2018(ኢዜአ)፡- በቦሌ በሻሌ ኮንዶሚኒየም ሲስተዋል የነበረውን የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት መቅረፍ ያስቻለ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ማከናወኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱ ለኢዜአ በላከው መረጃ፤ በቦሌ በሻሌ 40/60 ኮንዶሚኒየም የሚገኙ 6ሺህ 700 አባወራዎች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጿል።


 

ነዋሪዎቹን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ 6 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ መስመር ዝርጋታና 3 ባለ 800፣ 12 ባለ 630፣ 30 ባለ 1 ሺህ 250 ኪሎ ቮልት አምፔር በድምሩ 45 ትራንስፎርመር ተከላ ተከናውኗል ብሏል።

ቀደም ሲል ነዋሪዎቹ ባለ ሦስት ፌዝ ቆጣሪ በጋራ ይጠቀሙ ስለነበር የኃይል እጥረትና በኃይል መቆራረጥ ምክንያት ይቸገሩ እንደነበርም አስታውቋል።

በዚህም በተከናወነው የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ዝርጋታ ለእያንዳንዳቸው ቆጣሪ ተገጥሞላቸው ያልተቆራረጠ ኤሌክትሪክ እያገኙ መሆኑንም አረጋግጧል።


 

በተመሳሳይ በተለያዩ አካባቢዎች የነበረውን የኃይል መቆራረጥ ለመቀነስ ከአራብሳ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የሚነሱ አዳዲስ ወጪ መስመሮች ዝርጋታ ማከናወኑንም አስታውቋል።

ዝርጋታው የተከናወነላቸው ወጪ መስመሮች እያንዳንዳቸው ከ6 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት እንዳላቸው ገልጾ፤ ሁለቱ ባለ 33 ሺህ ቮልት ሶስቱ ደግሞ ባለ 15 ሺህ ቮልት ናቸው ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም