ኢትዮጵያን የሚገነባት እና የሚያጸናት የተደመረ ፍላጎትና ሀሳብ ነው - አቶ መለሰ ዓለሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን የሚገነባት እና የሚያጸናት የተደመረ ፍላጎትና ሀሳብ ነው - አቶ መለሰ ዓለሙ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያን የሚገነባትና የሚያጸናት የኢትዮጵያውያን የተደመረ ፍላጎትና ሀሳብ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ ገለጹ።
ብልፅግና ፓርቲ ለሀገራዊ መግባባት በምክክሩ የሚያደርገውን አዎንታዊ ተሳትፎ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል።
ለተሳካ የሀገረ መንግሥት ግንባታ መሠረት የሚጥሉ ጠንካራና ገለልተኛ የዳኝነትና ዴሞክራሲ ተቋማት መገንባት ተችሏል
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 የተቋቋመው፣ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉ መሠረታዊ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት እና በሕዝቦች መካከል የጋራ መግባባትን ለመፍጠር ነው።
ኮሚሽኑ አካታች የሆኑ የምክክር መድረኮችን በማመቻቸት ለዘላቂ ሰላም እና ለጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚረዱ ምክረ ሀሳቦችን የማቅረብ ግብም አለው።
ኮሚሽኑ ባለፉት ዓመታት በሀገር ውስጥ በየክልሎቹና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተወካዮች ልየታና የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራዎችን በስፋት አከናውኗል።
የብልፅግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ብልፅግና ፓርቲ ምክክር ኢትዮጵያን ጠንካራ ሀገር ያደርጋታል የሚል ፅኑ እምነት እንዳለው ገልፀዋል።
ብልፅግና ፓርቲ በሀገራዊ ምክክር የእስካሁን ሂደት ውስጥ ግልፅ የሆነ አዎንታዊ ሚና እየተወጣ መቆየቱንም አስታውሰዋል።
የምክክር ሂደት ለዘመናት የተሻገረና ከሀገረ መንግስት ግንባታ ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም በዘመናት መካከል በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያን የሚገነባትና የሚያጸናት የኢትዮጵያውያን የተደመረ ፍላጎትና ሀሳብ ነው ያሉት አቶ መለሰ፤ ፓርቲው ምክክርን የአንድ ወገን ሥራ አድርጎ እንደማይመለከተውም ተናግረዋል።
ምክክሩ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ጉዳይ መሆኑን በማመን፣ ፓርቲው በውይይት በመሳተፍና ለሀገረ መንግስት ግንባታ ይበጃሉ ያላቸውን አጀንዳዎች በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
እንደ ገዥ ፓርቲም ሂደቱ እንዲሳካ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ሚናውን እየተወጣ መሆኑን አክለዋል።
የምክክር ሂደቱ ለስምንት ወራት መራዘሙ ኮሚሽኑ ሥራውን በአግባቡና በጥራት እንዲያጠናቅቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።
ብልፅግና ፓርቲም በቀጣይ ወራት ለሀገራዊ መግባባት እየተካሄደ ላለው ምክክር አዎንታዊ ተሳትፎ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በዚህም ፓርቲው ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ የመግባባት ደረጃ ላይ እንድትደርስ ይሰራል ብለዋል።
ብልፅግና ፓርቲ የምክክር ሂደት ለትውልድ የሚኖረውን የላቀ ፋይዳ በሚገባ የሚገነዘብ በመሆኑ አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ሁሌም ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።