ቀጥታ፡

የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከፋሲል ከነማ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 25 /2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ዛሬም ቀጥሎ ሲውል አራት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።  

ከቀኑ 9 ሰዓት ሲዳማ ቡና ከፋሲል ከነማ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ የተመልካቾችን ትኩረት ስቧል።

ሲዳማ ቡና በሊጉ ካደረጋቸው 21 ጨዋታዎች መካከል 10ሩን ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በዘጠኝ ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በ21ዱ ጨዋታዎች ላይ 26 ጎሎችን ሲያስቆጥር 11 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

ቡድኑ በ39 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል።

ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ በሊጉ 21 ጨዋታዎችን አድርጎ በስምንቱ አሸንፎ በአራቱ ተሸንፎ በቀሪ ስምንት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 16 ግቦችን ሲያስቆጥር 13 ጎሎችን አስተናግዷል።

ፋሲል ከነማ በ33 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል።

ሲዳማ ቡና ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ እና የሊጉን መሪነት ለማጠናከር ይጫወታል።

ፋሲል ከነማ ካሸነፈ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ይመለሳል።

በሌላኛው መርሐ-ግብር ወላይታ ድቻ ከሃዋሳ ከተማ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

ወላይታ ድቻ እስከ አሁን በሊጉ 21 ጨዋታዎችን አድርጎ አራት ጊዜ ሲያሸንፍ ሰባት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ 10 ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። 22 ግቦችን ሲያስቆጥር 24 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ22 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ተጋጣሚው ሃዋሳ ከተማ በበኩሉ በሊጉ ባከናወናቸው 21 ጨዋታዎች በ10ሩ ሲያሸንፍ በአምስቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በስድስር ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 24 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 13 ግቦች ተቆጥረውበታል።

የሁለት ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ሃዋሳ ከተማ በ36 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። 

ወላይታ ድቻ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ እና ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት ይጫወታል።

ተጋጣሚው ሃዋሳ ከተማ ድል ከቀናው ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ይመለሳል።

ሁለቱ ጨዋታዎች በዋንጫ ፉክክሩ ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ናቸው። 

ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከባህር ዳር ከተማ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ኢትዮጵያ ቡና በ26 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል።

ባህርዳር ከተማ በ27 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

ኢትዮጵያ ቡና ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ፣ ባህርዳር ከተማ በ21ኛ ሳምንት በአርባምንጭ ከተማ ካስተናገደው ሽንፈት በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ።

አርባምንጭ ከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በሊጉ ሁለት ድሎችን ብቻ ያስመዘገበው አርባምንጭ ከተማ በ16 ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃ ይዟል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ28 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ጨዋታው አርባምንጭ ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም