በክልሉ የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎችን ውጤታማ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ውጤት እያስገኘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎችን ውጤታማ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ውጤት እያስገኘ ነው
ሀዋሳ፤ የካቲት 24/2018 (ኢዜአ)፦በሲዳማ ክልል የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎችን ውጤታማ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የተጀመረው ሥራ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ፡፡
የክልሉ የሥራ ዕድል ፈጠራ ምክር ቤት የ2018 በጀት ዓመት የሰባት ወራት የሥራ አፈጻጻም ግምገማ ተካሂዷል።
በለውጡ ዓመታት በሸበሌ ዞን፣ ጎዴ እና ደገሃቡር ከተሞች ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ እንደገለጹት፡ ባለፉት ሰባት ወራት በሥራ ዕድል ፈጠራ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው፡፡
በበጀት ዓሙቱ ለ71 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ በእስካሁን ሂደት ለ 55 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
የክልሉ መንግስት የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸውን ዜጎች ውጤታማ ለማድረግ ከስልጠና ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የጀመረው ሥራ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎች በተሰማሩበት የሥራ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ አጫጭር ስልጠናዎች ከመስጠት ባለፈ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በቀሪ ወራትም ለክልሉ ወጣቶች የመሸጫና የማምረቻ ቦታዎችን እንዲሁም የገንዘብ ብድር በማመቻቸት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ነው ያስታወቁት።
የክልሉ ሥራ፣ ክህሎትና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀገረፅዮን አበበ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ሥራ የተፈጠረላቸውን ዜጎች ውጤታማ ለማድረግ ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
ከተለመደው አሰራር በመውጣት ባለድርሻ አካላት የሥራ ዕድል ፈጠራን በባለቤትነት እንዲመሩ በመደረጉ የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎችን የሀብት ባለቤት በማድረግ ረገድ አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተገኝቷል ያሉት ደግሞ የቢሮው ምክትልና የሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ከፍያለው ከበደ ናቸው፡፡
በዚህም ወደስራ ለሚገቡ ወጣቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ስልጠናና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፣ ከ4ሺህ 400 በላይ ዜጎችም የውጭ ሃገር የሥራ ስምሪት አግኝተዋል ብለዋል።
በክልሉ ከተፈጠረው የሥራ ዕድል 60 በመቶ የሚሆነው በግብርና ዘርፍ መሆኑን የገለጹት ምክትል ቢሮ ሃላፊው፣ በግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በርካታ ወጣቶች ተሰማርተዋል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ለነባር ኢንተርፕራይዞች የስልጠና፣ የብድር፣ የመስሪያና የመሸጫ ቦታ ድጋፍ ከመደረጉ በተጨማሪ የገበያ ትስስር በመፍጠር አቅማቸውን የማሳደግ ሥራ መሰራቱንም ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ከክልል እስከ ወረዳ ባሉ መዋቅሮች የተውጣጡ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል፡፡