የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) ከአፍሪካ ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) ከአፍሪካ ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 24/2018 (ኢዜአ)፦ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) ከአፍሪካ ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።
ውይይቱ የተደረገው 130ኛው የዓድዋ ድል በዓልን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ በተካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች ኮንፈረንስ ጎን ለጎን ነው።
የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ከመጡ የመከላከያ ሚኒስትሮችና የልዑካን ቡድን መሪዎች ጋር ውጤታማ የሁለትዮሽ ውይይቶችን ማድረጋቸውን ኢዜአ ከመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
በውይይቱ ወቅት ቀደም ሲል በሀገራቱ መካከል የተፈረሙ የትብብር ስምምነቶች ያሉበት የአፈፃፀም ደረጃ በጥልቀት የተገመገመ ሲሆን፣ በቀጣይም ትብብሩን ይበልጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችሉ አዳዲስ የመግባቢያ ሰነዶችን ጨምሮ በልዩ ልዩ የሥራ መስኮች ላይ በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ ተደርሷል።
ሚኒስትሯ በውይይቱ ወቅት እንደገለፁት፤ የዓድዋ ድል ከታሪካዊ ፋይዳው ባሻገር ዛሬ አፍሪካ ከፊቷ የተደቀኑባትን ወቅታዊ የፀጥታና የደኅንነት ስጋቶች በጋራ ለመመከት እንደ ትልቅ የመንፈስ ምንጭና የትብብር ማዕቀፍ ሊያገለግል ይገባል።
በመሆኑም የአህጉሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ የሚያስችል የጋራ ግንዛቤ በመያዝ፣ በአንድነትና በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በተለይም በወታደራዊ ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሥልጠናና በልምድ ልውውጥ መስኮች በጋራ ለመሥራት መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን፣ ሽብርተኝነትንና ድንበር ተሻጋሪ የፀጥታ ስጋቶችን በጋራ ለመከላከል የሚያስችሉ ስልታዊ የትብብር አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል።
በውይይቱ የተሳተፉት የአፍሪካ ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለአህጉራዊ ሰላምና መረጋጋት እያበረከተች ያለውን ቀዳሚና የማይተካ ሚና አድንቀዋል።
የጥቁር ሕዝቦች ኩራት የሆነውን የዓድዋ ድል በዓልን በኢትዮጵያ ተገኝተው ከወንድሞቻቸው ጋር በጋራ በማክበራቸው የተሰማቸውን ጥልቅ ደስታ ገልፀው፣ በቀጣይም በጋራ የመከላከል አቅም ግንባታ ላይ በቁርጠኝነት ለመሥራት ያላቸውን ፅኑ ፍላጎት አረጋግጠዋል።
የሁለትዮሽ ውይይቱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነት ከማሳደጉም ባለፈ፣ የአህጉሪቱን የጋራ ደኅንነትና ትስስር ለማረጋገጥ የሚደረገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑ ተገልጿል።
ሚኒስትሯ ውይይት ካደረጉባቸው ሀገራትና ተቋማት መካከል የኬንያ፣ የደቡብ ሱዳን፣ የዚምባብዌ፣ የዛምቢያ፣ የኮንጎ ሪፐብሊክ ፣የቦትስዋና፣ የሩዋንዳ፣ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ የካሜሩን፣ የማሊ እና የአልጄሪያ የመከላከያ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ ጄኔራሎች እንዲሁም የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ከፍተኛ አመራሮች ይገኙበታል።