በሸገር ከተማ የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያመጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሸገር ከተማ የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያመጡ ነው
ሸገር፤ የካቲት 24/2018 (ኢዜአ)፦በሸገር ከተማ የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያመጡ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ጤና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የከተማው ጤና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበራ ቦቶሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከተማው በጤናው ዘርፍ ይታዩ የነበሩ የፍትሃዊ ተደራሽነት፣ የግብዓት አቅርቦት፣ የፋይናንስ አጠቃቀምና የዲጂታላይዜሽን ክፍተቶች በጥናት ተለይተው ወደ ሥራ ተገብቷል።
በዚህም ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የሰለጠነ የሰው ኃይል የማሟላትና ዘመናዊ የላቦራቶሪ መሣሪያዎችን የመትከል ሥራ በሰፊው ተከናውኗል።
በተለይም የመድኃኒት አቅርቦትን ለማሻሻል በተሰራው ሥራ ከጤና ጣቢያዎች በተጨማሪ የማህበረሰብ ፋርማሲዎችን በማስፋፋት፣ ሕብረተሰቡ መድኃኒት በተመጣጣኝ ዋጋ በቅርብ እንዲያገኝ መደረጉን አቶ አበራ ገልጸዋል።
የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ቁጥር በመጨመርም የአገልግሎቱ ተደራሽነት እንዲሰፋ መደረጉን አክለዋል።
በኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ የቱሉ ዲምቱ ጤና ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ በቀለ ጦጦው በበኩላቸው፤ ጤና ጣቢያው የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስፈልገውን መድኃኒት፣ የሕክምና ቁሳቁስና የሰው ኃይል ማሟላቱን ገልጸዋል።
በተለይም ለእናቶችና ሕፃናት ልዩ ትኩረት መሰጠቱን የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ፤ ወላድ እናቶችን ከቅድመ ወሊድ እስከ ድህረ ወሊድ ያለውን ክትትል በቴክኖሎጂ በመታገዝ በብቃት እያገለገሉ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የቱሉ ዲምቱ ጤና ጣቢያ ተገልጋዮች በበኩላቸው፤ በሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ማየታቸውን ገልጸዋል።
ከተገልጋዮቹ መካከል አቶ ሀብታሙ ዲታ፤ በጤና ጣቢያው የአገልግሎት አሰጣጡ በየጊዜው እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
''ባለቤቴ በዚሁ ጤና ጣቢያ የወሊድ ክትትል ስታደርግ ቆይታ፤ በወሊድ ሂደቱም የተሻለ አገልግሎት አግኝታለች'' ብለዋል።
ሌላዋ ተገልጋይ ወይዘሮ ኢትዮጵያ ጎጎላ በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል የነበሩ የአገልግሎት ክፍተቶች በመቃለላቸው በአሁኑ ወቅት የተሟላ ሕክምና በቅርብ እያገኙ መሆኑን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።