ቀጥታ፡

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጥናት ላይ የተመሰረቱ አማራጮችን ይዘው ሊቀርቡ ይገባል

ወላይታ ሶዶ፤ የካቲት 24/2018(ኢዜአ)፦ በመጪው ጠቅላላ ምርጫ የሚሳተፉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክንያታዊና በጥናት ላይ የተመሰረተ አማራጮችን ይዘው ሊቀርቡ እንደሚገባ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን አመለከቱ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓም ለማካሄድ ቀነ ቀጠሮ መያዙ የሚታወቅ ሲሆን ተወዳዳሪ ፓርቲዎችም ቅስቀሳን ጨምሮ የተለያዩ ቅድመ ምርጫ ዝግጅቶችን እያደረጉ ነው።

በጉዳዩ ዙሪያ ኢዜአ ያነጋገራቸው በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን እንዳሉት በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚሳተፉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህዝቡን የሚጠቅሙ አማራጭ ሃሳቦችንና ፖሊሲዎችን ይዘው በመቅረብ መወዳደር አለባቸው።

በዩኒቨርሲቲው የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ እሸቱ ተስፋዬ ምርጫ ዜጎች ዴሞክራሴያዊ መብታቸውን የሚጠቀሙበትና የዴሞክራሴያዊ ስርዓት ማሳያ መሳሪያ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ለ7ኛ ጊዜ ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት ላይ መሆኗን ጠቅሰው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዘላቂነት የህዝብንና የሀገርን ችግር በሚፈቱ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባቸዋል ነው ያሉት።

በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንዲሁም በዲፕሎማሲያዊ ዘርፎች ሃሳባቸውን ሸጠው በዴሞክራሴያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ ሚናቸውን መወጣት እንደሚገባቸውም አንስተዋል።

የቅድመ ምርጫ ወቅት የክርክሮችና ውይይቶች የዴሞክራሲ፣ የስልጣኔ መገለጫዎች መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ግንዛቤ የመፍጠሩ ስራ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የሰላምና ደህንነት ትምህርት መምህርና ተመራማሪ ወንድሙ አዴ ናቸው።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለህዝብና ለሀገር የሚበጁ አማራጭ ሀሳቦችን፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ይዘው በመቅረብ ማስተዋወቅ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

በምርጫ ቅስቀሳ እና ክርክር ወቅት በሰለጠነ መንገድ ከተንቀሳቀሱ ህዝቡም ድምጹን እንደሚሰጥ ጠቁመው የምርጫ ህጉንና ዕውቀትን መሠረት ባደረገ መልኩ ክርክሮች ሊደረጉ ይገባል ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም