ቀጥታ፡

የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ድጋፋችንን እናጠናክራለን - ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች

ሀዋሳ፤ የካቲት 24/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጉዳይ በመሆኑ ምላሽ እንዲያገኝ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ። 

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ታሪካዊ እና ሕጋዊ መሰረት ያለው ከመሆኑም በላይ የሉዓላዊነትና የትውልዱ የሕልውና ጉዳይ ነው።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች እንዳሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምን በተመለከቱ ጉዳዮች የጋራ አቋም ይዞ መስራት ከሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ(ኢዜማ) ፓርቲ ደቡብ ቀጠና ሲዳማ ክልል ማስተባበሪያ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ሀረገወይን ዘሪሁን ፓርቲያቸው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምን በሚያስከብሩ ጉዳዮች ላይ ፅኑ አቋም ይዞ ይሰራል ብለዋል።

ብሔራዊ ጥቅምን የሚያሳድጉ ማናቸውም የልማት ሥራዎችና ጥረቶች ለነገው ትውልድ የሚጠቅሙና የሚሻገሩ በመሆናቸው ስኬታማ እንዲሆኑ ፓርቲው የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ነው የገለጹት።


 

የሲዳማ አንድነት ፓርቲ(ሲአፓ) ሊቀ መንበር ለማ ሆያቶ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ያጣችው በአንድ ወቅት በተፈጠረ ታሪካዊ ስህተትና የፖለቲካ ሴራ ነው፤ በዚህም ላለፉት በርካታ ዓመታት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጉዳት ስናስተናግድ መቆየቷ የሚያስቆጭ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን እስከመጨረሻው ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ነው የሚገልጹት።

በብልፅግና ፓርቲ ሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊና የክልሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ ኤርሚያስ ኢትዮጵያ በሴራ ያጣችውን የባሕር በር ለማስመለስ ያለልዩነት መስራት ያስፈልጋል።


 

ኢትዮጵያ አሁን ካላት የህዝብ ቁጥርና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ አኳያ የገጠሟትን ተግዳሮቾች ለመፍታት የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ ማግኘት የግድ ነው ብለዋል።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ የምክር ቤቱ አባላት በኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ አቋም መያዛቸውንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም