ቀጥታ፡

ትውልዱ ከዓድዋ ድል ቁርጠኝነትን በመማር ሀገርን የማሻገር ታሪክ ሊደግም ይገባል

አዳማ፤የካቲት 23/2018 (ኢዜአ)፡- ትውልዱ ከዓድዋ ድል ቁርጠኝነትን በመማር ሀገርን ለማሻገር በልማት መስኩ ታሪክ ሊደግም እንደሚገባ በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የሜካናይዝድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ከፍያለው አምዴ ተናገሩ።

የአድዋ ድል 130ኛ ዓመት በዓልን ምክንያት በማድረግ በአዳማ ከተማ የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን በመድረኩ ላይ ሌተናል ጄኔራል ከፍያለው አምዴ፣ የአዳማ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ማቲያስ ሰቦቃ እና ከአዳማ ከተማ የተወጣጡ ወጣቶች ተሳትፈዋል።


 

በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የሜካናይዝድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ከፍያለው አምዴ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት፤ የአሁኑ ትውልድ የዓድዋን ድል አንድነት እና ቁርጠኝነትን መማር አለበት።

በተለይም ከለውጡ ወዲህ ወጣቶች የድሉን ታሪክ እንዲያውቁና እንዲጠብቁ የተደረገው ጥረት ድሉን ኢትዮጵያን ለማበልጸግ መጠቀም እንደሚቻል ያመላከተ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሌተናል ጄኔራል ከፍያለው አክለውም፤ ትውልዱ አባቶቻችን ያስረከቡንን ታሪክ ለማስቀጠል በኢኮኖሚ፣ በሰላም፣ በፖለቲካና በዲፕሎማሲ ረገድ ከእኛ ምን ይጠበቃል የሚለውን በአግባቡ ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል። 

ወጣቱ በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ግንባር ቀደም ሚና መጫወት እንዳለበትና ለዚህም የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ በልማት ስራዎች ላይ ሊረባረብ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአዳማ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ማቲያስ ሰቦቃ በበኩላቸው፤ የኦሮሞ ህዝብ በአድዋ ድል ውስጥ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር በመሆን ለሀገሩ ሉዓላዊነትና ማንነት የማይተካ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል። 


 

የአድዋ ድል የሀገር ፍቅርና የአንድነት ምልክት ከመሆኑም ባለፈ የኢትዮጵያ ህዝቦች የጋራ ታሪካዊ አሻራ መሆኑን ትውልዱ ሊረዳው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ለዚህም ወጣቱ የከተማዋንና የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ የተጀመሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች ግባቸውን እንዲመቱ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።


 

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ሲሳይ አበራ፤ አድዋ የጥቁር ህዝቦች ኩራትና ኢትዮጵያ በዓለም የምትታወቅበት ታላቅ አሻራ መሆኑን ገልፆ ድሉ የምንኮራበት መገለጫችን ነው ሲልም ተናግሯል። 

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት አብደላ ጌሎ በበኩሉ፤ "አባቶቻችን በከፈሉት ተጋድሎ ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ ሀገር ተረክበናል" ብሏል።

ውይይቱ ወጣቶች ስለ አድዋ ድልና ስለ ማንነታቸው ጥልቅ ግንዛቤ እንዲያገኙ ትልቅ ዕድል መፍጠሩንም ገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም