የዓድዋ ብሩህ መንፈስ የሚጸየፈውን ቅጥረኝነትን በማስወገድና ብሔራዊ ጥቅምን በማስቀደም ኢትዮጵያን ከፍ እናድርግ - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ብሩህ መንፈስ የሚጸየፈውን ቅጥረኝነትን በማስወገድና ብሔራዊ ጥቅምን በማስቀደም ኢትዮጵያን ከፍ እናድርግ - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 23/2018(ኢዜአ)፦ የዓድዋ ብሩህ መንፈስ የሚጸየፈውን ቅጥረኝነትን በማስወገድና ብሔራዊ ጥቅምን በማስቀደም ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ከፍ እናድርግ ሲሉ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ጥሪ አቀረቡ።
ፕሬዝዳንቱ “ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ” በሚል መሪ ሀሳብ በተከበረው 130ኛው የዓድዋ ድል በዓል ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ መንገድ ሁሉ ብሩህ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ታዬ፤ በመልዕክታቸው አሁን ላለንበት ወቅት መሠረታዊ ናቸው ያሏቸውን ሦስት ዋና ዋና የዓድዋ ድል ተምሳሌቶችን ለሕዝብ ይፋ አድርገዋል።
የመጀመሪያው ተምሳሌት ልጓም ከሌለው የፖለቲካ ምኞት ወይም ናፍቆት ይልቅ ለሕዝብ ፍቅርና ለወገን ሕይወት መለወጥ መጽናት ነው ብለዋል።
ሁለተኛውና ቁልፍ ጉዳይ ደግሞ ለውጭ ኃይላት ድርጎ ከመማለል ወይም ከጋሻ ጃግሬነት ይልቅ ለሀገርና ለብሔራዊ ክብር መታመን መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
"ከዚህ በላይ ጸጋ፣ ከዚህ በላይ ክብር የለም" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የዓድዋ ብሩህ መንፈስ የሚጸየፈው ቢኖር ቅጥረኝነትን ብቻ መሆኑን አንስተዋል።
በሦስተኛ ደረጃ፤ ከአፍታና ከዕለታዊ የፖለቲካ ስሌት ይልቅ የሕዝብን መብት ያማከለ ስትራቴጂካዊ ዕይታን መተለምና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅሞች ማዕከል ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያን የዕድገት ግስጋሴ ለማወክ በየጊዜው የሚመላለሱ ኃይሎችን መግራት ተገቢ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ፕሬዝዳንቱ በሀገሪቱ የመዘመን ጎዳና ላይ የተጋደሙ ካሉ አልፎ መጓዝ ወይም ተራምዶ መሻገር እንደሚገባ ገልጸዋል።
ከማያድግ ወይም ከቆመ ሐሳብ ጋር ውል ያሰሩ ካጋጠሙ ደግሞ ይስተካከሉ ዘንድ ጊዜ መስጠት እንደሚያስፈልግና ወደ ኋላ መመለስ እንደማይገባ አስታውቀዋል።
የዘመናዊነትን ሀሳብ የናቀ የፖለቲካ ሰው ለምክንያታዊነት ራሱን ተገዥ ያደርጋል ብሎ ለማሰብ ብርቱ ትዕግሥትና ጽናት እንደሚጠይቅ ነው የጠቀሱት።
ኢትዮጵያ የምታሸንፈው በልጆቿ ብርታትና በሀሳቧ ልዕልና ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የሀሳብና የእውቀት ትግሉ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።
በጥቁር ሕዝቦች ዘንድ "ሰው በሰውነቱ ነፃ ነው" በሚል በተቀመጠው የኢትዮጵያ የመገለጥ ድርሳን እና ኢትዮጵያን ዓለም ባደነቃት ልክ ከፍ ልናደርጋት ይገባል ብለዋል።
በዱር በገደሉና በየምሽጉ ለሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ባስተላለፉት ጥሪ የዓድዋ አደራ ኢትዮጵያን ማጽናትና በዓለም አደባባይ ከፍ ማድረግ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህንኑ ብሔራዊ መልሕቅ አበርትተው እንዲይዙም ነው አፅንኦት የሰጡት።