የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት መርሃ ግብሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት መርሃ ግብሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 23/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት መርሃ ግብሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ በምሳሌነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ገለጹ።
የዓለም አቀፉ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና አውደ ጥናት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን በዚሁ ወቅት እንዳሉት የዓለም አቀፉ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም በዓለም ደረጃ የአካባቢ መራቆትን፣ የብዝሃ ህይወት መመናመንን እንዲሁም በትልልቅ የውሀ አካላት ላይ እየደረሱ ያሉ ጉዳቶችን ለመከላከል ድጋፍ የሚያደርግ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው።
ተቋሙ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት የሚሆን ፕሮግራም ተግባራዊ እንደሚያደርግ ገልጸው የአውደ ጥናቱ ዓላማ ከዚህ ቀደም የተተገበሩ ፕሮግራሞችን ለመገምገም መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በብዝሃ ህይወት ጥበቃ እና የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ተግባራዊ መደረጋቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት መርሃ ግብሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ በምሳሌነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በእነዚህ ስራዎች አማካይነት እውቅና እያገኘችበት እንደምትገኝም ገልጸዋል።
የዓለም አቀፉ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም የአፍሪካ አስተባባሪ ጆንኪ ቴኑ በበኩላቸው የምስራቅ አፍሪካ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት እና እምቅ አቅም እንዳለው ጠቅሰው፥ ይሁን እንጂ እንደ ብዝሃ-ህይወት መጥፋት፣ የመሬት መራቆት እና ብክለት ያሉ ፈተናዎች የተደቀኑበት ቀጣና ነው ብለዋል።
በመሆኑም ቀጣናዊና፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት በአየር ንብረት ለውጥ የሚደርሱ ጫናዎችን ለመቋቋም በትብብር መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የዓለም አቀፉ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በተለያዩ መንገዶች የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።