ትውልዱ አባቶች በአድዋ የፈፀሙትን አኩሪ ታሪክ ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ሊደግመው ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ትውልዱ አባቶች በአድዋ የፈፀሙትን አኩሪ ታሪክ ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ሊደግመው ይገባል
ባህር ዳር፡ የካቲት 23/2018 (ኢዜአ)፡- ትውልዱ አባቶች በአድዋ የፈፀሙትን አኩሪ ታሪክ ሰላም፣ ልማትና አንድነትን በማጠናከር ሊደግመው እንደሚገባ የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ገለጸ።
130ኛው የአድዋ የድል መታሰቢያ በዓል "ከአኩሪ ታሪክ፤ ወደ ብሩህ አድማስ" በሚል መሪ ሀሳብ በባህር ዳር ከተማ ተከብሯል።
የቢሮ ኃላፊው አቶ መልካሙ ፀጋዬ በበዓሉ ላይ እንደገለጹት፤ ጀግኖች አባቶቻችን በአድዋ የከፈሉት መስዋዕትነት ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ከፍ ብላ እንድትታይ አስችሏል።
"ድሉ የአባቶቻችን የጽናት ምልክት፣ የሉዓላዊነታችን ማስከበሪያና የማንነታችን መገለጫ ነው" ያሉት አቶ መልካሙ፤ ድሉ የአመራር አንድነትና የጋራ ጥበብ የታየበት መሆኑንም ገልጸዋል።
ሀገራዊ ፍላጎታችንንና ጥቅሞቻችንን ለማሳካት ልዩነትን ወደ ጎን በመተው በጋራ ራዕይ መመራት ብቸኛው አማራጭ መሆኑን ከአድዋ ድል መማር እንደሚገባም አሳስበዋል።
የአሁኑ ትውልድ የተጀመረውን የለውጥና የዕድገት ጉዞ ማረጋገጥ የሚችለው የአድዋን አንድነትና ጥበብ መላበስ ሲችል መሆኑን ተገንዝቦ መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
ትውልዱ አባቶቻችን በአድዋ የፈፀሙትን አኩሪ ታሪክ ሰላም፣ ልማትና አንድነትን በማጠናከር ሊደግመው እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ዳኝነት አያሌው በበኩላቸው፤ የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።
ጀግኖች አባቶቻችን በአድዋ የፈፀሙት የጀግንነት ታሪክ ለመላው ጥቁር ህዝቦች ሁሉ የነፃነት ፋና ወጊ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል።
ይህ ድል በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ የአፍሪካ ሀገራት ለነፃነታቸው እንዲነሳሱ ትልቅ አቅም መፍጠሩን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፤ የዚህ ዘመን ትውልድም የሀገሩን አንድነትና ሉዓላዊነት የመጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል።
በበዓሉ አከባበር ስነ-ሥርዓት ላይ አባት አርበኞች፣ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የጸጥታ ኃይሎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።