ቀጥታ፡

ትውልዱ ከዓድዋ ጀግኖች የአንድነትና የአይበገሬነት መንፈስ በመማር በልማት የራሱን ታሪክ ሊፅፍ ይገባል-ብሔራዊ የኢትዮጵያ ሰራዊት ማሕበር

ወላይታ ሶዶ፣ የካቲት 23/2018(ኢዜአ):-የአሁኑ ትውልድ ከዓድዋ ጀግኖች የአንድነትና የአይበገሬነት መንፈስ በመማር በልማት መስክ የራሱን አዲስ ታሪክ ሊጽፍ ይገባል ሲሉ በብሔራዊ የኢትዮጵያ ሰራዊት ማሕበር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ታምራት ሞላ ገለፁ፡፡

መቶ አለቃ ታምራት ሞላ ለኢዜአ እንደገለጹት፤የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀን ወራሪ ኃይል ድል በማድረግ ሉዓላዊነታቸውን ያስከበሩበት የብሔራዊ አንድነት ምልክት መሆኑንም አንስተዋል።

ዓድዋ ኢትዮጵያውያን ለወራሪ ኃይል አለመገዛታቸውን በተግባር ያሳዩበትና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ጮራ የፈነጠቁበት የድል ቀንዲል መሆኑንም አንስተዋል።

ማሕበሩ የዓድዋ ጀግኖችን ታሪክ ለትውልዱ በማስተዋወቅ ተተኪ ጀግኖችን ለማፍራት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ወጣቱ ትውልድ የሀገሩን ሰላምን በማጽናትና ልማትን በማፋጠን ግንባር ቀደም ሚናውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

የዓድዋ ድል የትላንት ኩራት ብቻ ሳይሆን ለዛሬ ትውልድ የልማት ጉዞ ሞተር መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።

አርበኛ ባሻ ተክሌ ታደሰ ዓድዋ የደምና የአጥንት መስዋዕትነት የተከፈለበት ታላቅ የድል ታሪክ መሆኑን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የጀግኖች ሀገር መሆኗን የገለጹት አርበኛው፣ ይህንን ክብር ለማስቀጠል ልዩነቶችን ወደ ጎን ትቶ በጋራ መቆም ይገባል ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት የክብር ተሰናባች አባል ሻለቃ ጳውሎስ ገብረስላሴ በበኩላቸው፣ የዓድዋ ድል የቅኝ ግዛት እሳቤን ያከሰመና የኢትዮጵያውያንን የሀገር ፍቅር ለዓለም ያስመሰከረ መሆኑን ተናግረዋል።

ጀግኖች አባቶች በባህላዊ መሣሪያ ዘመናዊውን የጣልያን ጦር ድል በማድረግ ነጻ ሀገር እንዳቆዩልን በማስታወስ፣ የአሁኑ ትውልድ ይህንን የጀግንነት ታሪክ ለቀጣዩ ትውልድ ማውረስ አለበት ብለዋል።

የሀገርን ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት ማስከበር እና ድህነትን ማሸነፍ የአርበኞችን ገድል በልማት መድገም መሆኑንም አመልክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም