ቀጥታ፡

አድዋ የኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ ድልና የጥቁር ህዝቦች የነፃነት አርማ ነው

ድሬዳዋ፣ የካቲት 23/2018 (ኢዜአ):- አድዋ የኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ ድልና የመላው ጥቁር ህዝቦች የነፃነት አርማ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የድሬዳዋ ወጣቶችና ሴቶች ተናገሩ።

በድሬዳዋ የሚገኙ ወጣቶችና ሴቶች 130ኛው የአድዋ ድል በዓልን በፓናል ውይይት አክብረዋል።

በበዓሉ ላይ የተሳተፉት ወጣቶች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አድዋ የኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ ድልና የመላው ጥቁር ህዝቦች የነፃነት አርማ ነው።

ወጣት ሰርካለም መለስ ፤ የአድዋ ድል ጀግኖች አባቶች ለሀገር ክብርና ሉአላዊነት በአንድነት በከፈሉት መስዋዕትነት የተገኘ የጀግንነት ውጤት መሆኑን ተናግራለች። 

ይሄን የአባቶች የሀገር ፍቅርና አይበገሬነት ወኔ በማንገብ የአሁኑ ትውልድ የኢትዮጵያ ከፍታ ለማረጋገጥ በአንድነት ልንተጋ ይገባል ብላለች።

ወጣት አህመድ ሙሴ በበኩሉ የአድዋ ድል የአሁኑ ትውልድም በአንድነት የሀገርን ሰላም እና ልማት ለማረጋገጥ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አርአያ እንደሚሆን ገልጿል።

እንደ ጀግኖች አባቶች ሁሉ ትውልዱም በአንድነት በመሰለፍ በህዳሴው ግድብ፣ በሀገራዊ የልማት ኢንሼቲቮች፣ በኮሪደር ልማት፣ በዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ስራዎች ላይ የራሱን ዘመን ተሻጋሪ ድል እያስመዘገበ መሆኑን አንስቷል።

ወጣቶች የአድዋን ድል ያከበርነው የአባቶቻችንን ህብረት፣ ሀገራዊ ፍቅርና የአልሸነፍም ወኔያቸውን በመላበስ ነው ያለው ደግሞ  ወጣት ቅዱስ ተከስተ ነው። 

ወጣት ቅዱስ እንደገለፀው፤ አገራችን አሁን የምትፈልገው በጀግንነት ከድህነትና ከኋላቀርነት በመውጣት ከፍታዋን ዕውን ማድረግ ነው።

ለዚህም ወጣቶች በተቀናጀ መንገድ ልንተጋ ይገባል ብሏል ።

ወይዘሮ ዲቃ ሚዛን በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሴቶች በአድዋ ጦርነት ወቅት ያሳዩትን ቁርጠኝነትና ወኔ በመለባስ ከድህነት ለመውጣት እየተጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይሄን ታላቅ ድል ስናከብር የጀመርነውን ከድህነት የሚሻገር ጉዞ ይበልጥ ለማጠናከር ያለንን ቁርጠኝነት በማሳየት ጭምር መሆን አለበት ብለዋል።


 

በበአሉ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው የአድዋ ድል ጀግኖች አያቶቻችንና አባቶቻችን  በአንድነት ተመው ዘመን የተሻገረ ህያው ድል ያስመዘገቡበት አኩሪ ታሪክ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከዚህ ደማቅና ሕያው የጥቁር ህዝብ አርማ በመማር ሀገርን ወደ ብልፅግና ማማ ለማሻገር የተጀመሩ ጥረቶችን ለማሳካት በቁርጠኝነት ልንረባረብ ይገባል ብለዋል።


 

በበዓሉ ላይ ከየወረዳው የተውጣጡ ወጣቶችና ሴቶች፣ የአገር መከላከያ እና የፖሊስ ሠራዊት አባላትና አመራሮች እንዲሁም የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም