ለአየር ንብረት ተስማሚ ግብርና ለቀጣናው ይዞት የመጣው ተስፋ - ኢዜአ አማርኛ
ለአየር ንብረት ተስማሚ ግብርና ለቀጣናው ይዞት የመጣው ተስፋ
በሙሴ መለሰ(ኢዜአ)
የአየር ንብረት ቀውስ በፍጥነት እያደገ ይገኛል። ይህም በቀጣናው ግብርና እና ስርዓተ ምግብ ላይ ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል። ኢ-ተገማች የዝናብ ሁኔታ፣ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚከሰቱ ድርቆች እና የመሬት መራቆት የግብርና ምርታማነትን በመቀነስ፣ በዜጎች ኑሮ ላይ ተጽእኖ በማሳደር እና የስርዓተ ምግብ ላይ ፈተና መሆኑን ቀጥሏል።
ግብርና በምስራቅ አፍሪካ ከ25 እስከ 40 በመቶ ዓመታዊ ጥቅል ምርት (ጂዲፒ) የሚሸፍን ነው።
የግብርናውን አብዛኛውን ድርሻ የሚወስዱት አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ናቸው። በነዚህ ሀገራት ግብርና ከፍተኛውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ድርሻ ይወስዳል።
በቀጣናው ያለው ግብርና አብዛኛው ዝናብ ላይ ጥገኛ በመሆኑ በየጊዜው ለሚቀያየረው የአየር ንብረት ሁኔታ እና አደጋዎች ተጋላጭ ነው።
ለአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ ስትራቴጂዎች እና ስልቶች መቅረጽና መተግበር ላይ ውስንነቶች አሉ።
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ጠንካራ የግብርና ስርዓት ለመገንባት በአፍሪካ ደረጃ እየተተገበሩ ካሉ ተግባራት መካከል አንዱ ለአየር ንብረት ተስማሚ ግብርናን ማስፋት ነው።
ለአየር ንብረት ተስማሚ ግብርና (Climate-smart agriculture) ሁሉን አቀፍ እይታ ያለው የግብርና ምርታማነት አማራጭ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ይህ የአሰራር ዘዴ የግብርና ምርታማነት ብቻ ሳይሆን ለአደጋዎች የማይበገር አቅም መገንባት እና ለአየር ንብረት ተስማሚ መሆን እንዳለበት ያስቀምጣል።
ጽንሰ ሀሳቡ ከተለምዷዊ የግብርና አሰራር በመውጣት ሳይንስ፣ ፖሊሲ፣ ፋይናንስ እና ቴክኖሎጂን በማጣመር ግብርናን የማይበገር፣ ዘላቂ እና የኢኮኖሚ ጠቀሜታውን ማላቅ እንደሚገባ ያመለክታል።
ምርታማነት እና ገቢ መጨመር፣ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም አቅም መገንባት እንዲሁም የማጣጣሚያ እቅዶችን መተግበርን ጨምሮ የበካይ ጋዞችን ልቀት መቀነስ ለአየር ንብረት ተስማሚ ግብርና ቁልፍ የሚባሉ ምሰሶዎች ናቸው።
በአየር ንብረት ተስማሚ ግብርና (Climate-smart agriculture) አማካኝነት በቆሎ፣ ስንዴ፣ ማሽላ እና ሌሎች ድርቅና ከፍተኛ ሙቀትን የሚቋቋሙ ሰብሎችን በመትከል ምርታማነትን የማሳደግ ስራ በአፍሪካ ደረጃ እየተከናወነ ይገኛል።
የውሃ እና አፈር አስተዳደርን ማሻሻል፣ ውጤታማ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እና ዲጂታል የአየር ንብረት የማማከር አገልግሎቶችን (digital climate advisory services) መስፋት ምርታማነትን በመጨመር እና አርሶ አደሮች በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔዎችን እንዲያሳልፉ እያገዘ ይገኛል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ የአፍሪካ የግብርና ትራንስፎርሜሽን የቴክኖሎጂ ኢኒሼቲቭ ከ13 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለአየር ንብረት ተስማሚ ግብርና እና ኢኖቬሽን ስራዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ያደረገ ሲሆን ምርት በ25 ሚሊዮን ቶን እንዲጨምር አስችሏል።
በኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ተስማሚ የሆኑ ኢኒሼቲቮችን በመተግበር ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ዜጎች ብዝሃ ህይወት እና አካባቢን እንዲጠብቁ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
አረንጓዴ አሻራ የዚሁ ስራ አንድ ማሳያ ነው።
ለአየር ንብረት ተስማሚ የሆነ ግብርና (Climate-smart agriculture) በምስራቅ አፍሪካ ላለው የአየር ንብረት ቀውስ እንደ ስትራቴጂካዊ ምላሽ መስጫ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ነው።
የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ዘላቂ ፈተና በሆነበት የአፍሪካ ቀንድ ይህ የግብርና አሰራር ዘዴ አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንደሆነ ይነሳል።
ድርቅን የሚቋቋሙ ሰብሎችን መጠቀም፣ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች፣ የተቀናጀ የደን ልማት ስራ፣ የውሃ አስተዳደርን ማሻሻል፣ አርብቶ አደሮች በሚኖርባቸው አካባቢዎች የማይበገር የአደጋ መቋቋም ስርዓትን ማጠናከር፣ የአየር ንብረት መረጃውን በወቅቱ ተደራሽ ማድረግ እና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓትን ማጠናከር እየተከናወኑ ካሉ ስራዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የምግብ ስርዓት የማይበገር ፕሮግራም (FSRP) ለአየር ንብረት ተስማሚ ግብርናን ማስፋት ትኩረት ከሰጣቸው አጀንዳዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ በአየር ንብረት ተስማሚ ግብርና እና የስርዓተ ምግብ ላይ ያተኮረ ቀጣናዊ ስብሰባ ይደረጋል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) በአፍሪካ ቀንድ ለአየር ንብረት ተስማሚ ግብርናን ማስፋት ላይ ያተኮረ ቀጣናዊ የምክክር ፎረም የካቲት 24 እና 25 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ያካሂዳል።
የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የሥርዓተ ምግብ አይበገሬነት ፕሮግራም ከዓለም ባንክ የአፍሪካ ቢሮ እና ከደቡባዊ አፍሪካ የግብርና ምርምር እና ልማት ማስተባበሪያ ማዕከል ጋር በመሆን ፎረሙን አዘጋጅተውታል።
ምክክሩ የአየር ንብረት ለውጥ ግብርና ላይ ተጽእኖ እያሳደረ ባለበት ወቅት የሚካሄድ መሆኑ ወቅቱን የጠበቀ እንደሚያደርገው ተገልጿል።
ከአደጋ ጊዜ ምላሾች ወደ ረጅም ጊዜ የማይበገር ስትራቴጂዎች እና ከሙከራ ጊዜ ኢኒሼቲቮች ወደ ቀጣናዊ መፍትሄዎች መሸጋገር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር እንደሚደረግ ኢዜአ ከኢጋድ ሴክሬተሪያት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
በፎረሙ ላይ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የልማት አጋሮች፣ ተመራማሪዎች እና የግሉ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ይሳተፋሉ።
በቀጣናው የሥርዓተ ምግብን ማጠናከር እና ለአየር ንብረት ተስማሚ ግብርናን ማስፋት የሚቻልባቸውን ተጨባጭ መፍትሄዎች እንደሚዳሠሡም ተመላክቷል።
የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የማይበገር፣ አካታች እና ኢንቨስትመንትን ማዕከል ያደረገ ጠንካራ የግብርና ሥርዓቶችን ከምግብ ምርታማነት እና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት ጎን ለጎን መገንባት የሚቻልበትን መደላድል መፍጠር ከፎረሙ የሚጠበቅ ዋና ውጤት ነው ተብሏል።
ቀጣናዊ ፎረሙ ኢጋድ ተጋላጭነትን ወደ እድል ለመቀየር እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለአየር ንብረት ተስማሚ ግብርና የተቀናጀ የተግባር ምላሽ ለመስጠትና ለግብርና ኢኖቬሽን ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይም አመልክቷል።
በአፍሪካ ቀንድ ሚሊዮኖች የአየር ንብረት ለውጥ በፈጠራቸው ቀውሶች ገፈት ቀማሽ በሆኑበት በአሁኑ ወቅት ለአየር ንብረት ተስማሚ ግብርና የቴክኒክ አማራጭ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው።
የግብርና አሰራር ዘዴው ለዘላቂ ልማት፣ ለኢኮኖሚ አይበገሬነት እና ማህበራዊ መረጋጋት አስፈላጊ የሆነ ስትራቴጂ እንደሆነም በዘርፉ ባለሙያዎች ይነሳል።
በአዲስ አበባ የሚካሄደው ቀጣናዊ ፎረም በአየር ንብረት ተስማሚ ግብርና የሀገራትን የፖለቲካ ቁርጠኝነት ለማረጋገጥ፣ ድንበር ተሻጋሪ ትብብርን ለማጠናከር እና ለአየር ንብረት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ያለውን የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ እንደ መልካም አጋጣሚ የሚታይ መድረክ ነው።
በተለይም ለአየር ንብረት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚከናወነው ስራ የማይበገር አቅምን ለመገንባት ቁልፍ ሚና ይጫወታል።
በቀጣናው የሚደረጉ ጥረቶች ከንግግር ባለፈ በተግባር ታግዘው ውጤታማ ከሆኑ ከተበታተኑና አደጋን ማዕከል ካደረጉ ምላሾች ወደ የማይበገር፣ አካታች እና መጪውን ጊዜ የዋጀ የግብርና እድገት መሸጋገር ይቻላል።