ትውልዱ የዓድዋን የድል መንፈስ በመላበስ የሀገሩን ሰላምና ዕድገት ማረጋገጥ አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ትውልዱ የዓድዋን የድል መንፈስ በመላበስ የሀገሩን ሰላምና ዕድገት ማረጋገጥ አለበት
አዲስ አበባ፤ የካቲት 23/2018(ኢዜአ)፦ ትውልዱ የዓድዋን የድል መንፈስ በመላበስ የሀገሩን ሰላምና ዕድገት ማረጋገጥ እንዳለበት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን የጎበኙ አርበኞችና የስካውት አባላት ገለጹ።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለ130ኛው የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
በልማት አርበኝነት የአዲሱ ዘመን የዓድዋ ድሎችን እያስመዘገብን ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አገልግሎቱ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር እና የአዲስ አበባ ስካውት ማኅበር አባላት የተቋሙን ዲጂታል ኤግዚቢሽን መጎብኘታቸውን ለኢዜአ በላከው መረጃ ገልጿል፡፡
የሀገር ሰላም፣ ደኅንነትና ዕድገት በትውልዶች ቅብብል የሚረጋገጥ መሆኑን የተናገሩት የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበርና የአዲስ አበባ ስካውት ማኅበር አባላት፤ የአሁኑ ትውልድ የዓድዋን የድል መንፈስ በመላበስ አዳዲስ ሀገራዊ ስኬቶች ማስመዝገብ እንዳለበት መናገራቸውን አስታውቋል፡፡
የስለላ ጥበብ ለዓድዋ ድል ከፍተኛ ሚና እንዳበረከተ አስታውሰው፤ በመረጃና ደኅንነት ተቋሙ የተከናወኑ የለውጥ ሥራዎችም ኢትዮጵያን ከየትኛውም ጠላት መከላከል የሚያስችል አቅም እንደተፈጠረ መተማመን እንዲሰማቸው ማድረጉን መጠቆማቸውንም ገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ስካውት ማኅበር አባል የሆኑ ተማሪዎችም የኢትዮጵያ ባለውለታ የሆኑ አርበኞች ስለከፈሉት መስዋዕትነትና ስላስረከቧቸው ነፃ ሀገር በማመስገን፤ የተሰጣቸውን አደራ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አርበኞቹና የስካውት አባላቱ ዓድዋ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ፀንታ እንድትቆም ያበረከተው አስተዋጽኦ ሁሌም የሚታወስ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የተውጣጡ ዜጎች ዘርና ሃይማኖት ሳይለዩ በአንድነት መቆማቸው ለድሉ አስተዋፅዖ ማበርከቱ ከፍተኛ ትምህርት የሚወሰድበት እሴት መሆኑን መናገራቸውንም አገልግሎቱ በመረጃው ጠቁሟል፡፡