አትሌቶች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ በማድረግ ሀገራቸውን ያስከበሩ ብሔራዊ ጀግኖቻችን ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
አትሌቶች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ በማድረግ ሀገራቸውን ያስከበሩ ብሔራዊ ጀግኖቻችን ናቸው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2018 (ኢዜአ)፦አትሌቶች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ በማድረግ ሀገራቸውን ያስከበሩ ብሔራዊ ጀግኖቻችን ናቸው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአንጋፋ አትሌቶች የመኖሪያ ቤትና የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አንጋፋ አትሌቶች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ በማድረግ ሀገራቸውን ያስከበሩ ብሔራዊ ጀግኖች ናቸው፡፡
እነዚህ አትሌቶች ለኢትዮጵያ ለከፈሉት ትልቅ ውለታ ህዝብና ሀገር ሁል ጊዜም እንደሚያከብሯቸውና እንደሚያመሰግኗቸው ተናግረዋል።
ይሁንና በህይወት መንገድ ውስጥ በሚያጋጥሙ ውጣ ውረዶች ምክንያት አትሌቶች ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሊጋለጡ እንደሚችሉ አንስተው፣ የከተማ አስተዳደሩም ይህንን ከግምት በማስገባት አንጋፋ አትሌቶችን መደገፉን አስረድተዋል።
ይህ ዓይነቱ ድጋፍ ቀጣዩ ትውልድ ሀገር ባለውለታዎቿን እንደማትረሳ በመረዳት የድርሻውን እንዲያበረክት ትልቅ ትምህርት እንደሚሰጥም ገልጸዋል።
ለአትሌቶቹ የተሰጠው የገንዘብ ድጋፍ በከተማው የሚገኙ የግል ባለሀብቶችን በማስተባበር የተገኘ መሆኑን ጠቅሰው፤ መሰል የሀገር ባለውለታዎችን የማስታወስ ስራ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን በበኩሉ፤ አንጋፋ አትሌቶች ያሉበትን ሁኔታ በመለየት ለከተማ አስተዳደሩ ያቀረቡት ጥያቄ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ በማግኘቱ ምስጋናውን አቅርቧል።
በዕለቱ የቤትና የገንዘብ ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል አትሌት ኮማንደር ጌጤ ኡርጌ የመኖሪያ ቤትና የ10 ሚሊዮን ብር እንዲሁም የህክምና ወጪ ድጋፍ ተደርጎላታል።
አትሌቷም በሰጠችው አስተያየት "ሀገሬ እንዳስታወሰችኝና እንዳከበረችኝ ተሰምቶኛል" ስትል ደስታዋን ገልጻለች።
በተመሳሳይ እያንዳንዳቸው የሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ የተበረከተላቸው አሰልጣኝ ዘውዴ ሀይለማርያም፤ አሰልጣኝ ሻለቃ ባሻ ግርማ ወልደሀና እና ሌሎች አንጋፋ አትሌቶች፤ አስተዳደሩ ያደረገው በጎ ተግባር ሀገር ባለውለታዎችን እንደምታመሰግን ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ መልዕክት የሚያስተላልፍ መሆኑን ገልጸዋል።