የኢትዮጵያ እና የአዘርባጃን የሁለትዮሽ ትብብር በተለያዩ ዘርፎች የበለጠ እየተጠናከረ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እና የአዘርባጃን የሁለትዮሽ ትብብር በተለያዩ ዘርፎች የበለጠ እየተጠናከረ መጥቷል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21 /2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን በተለያዩ መስኮች ያላቸው ትብብር ባለፉት ጥቂት ዓመታት እየተጠናከረ መምጣቱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የአዘርባጃን ይፋዊ የስራ ጉብኝት ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ልዑካቸው በፕሬዝዳንት ኢልሃም አሊዬቭ ግብዣ በአዘርባጃን ለሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ባለፉት ጥቂት ዓመታት የበለጠ እየተጠናከረ መምጣቱን ጠቅሰው በጉብኝቱ የልምድ ልውውጦች መደረጋቸውን አንስተዋል።
አዘርባጃን በኢትዮጵያ ኤምባሲ መክፈቷ ለሁለቱ ሀገራት ትብብር መጎልበት አስተዋጽኦ እንዳለውም አመልክተዋል።
የኢኮኖሚ ትብብሩን በአቪዬሽን እና በተለያዩ መስኮች ለማጠናከር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከአዘርባጃን አቻው ጋር ለመስራት የሀሳብ ልውውጦችን ሲያደርግ መቆየቱንም ነው ያወሱት።
በኢትዮጵያ እና በአዘርባጃን መሪዎች መካከል የተደረገው ውይይትም የሀገራቱ የግንኙነት ደረጃ ከፍ ማለቱን የሚያሳይ መሆኑን አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከአዘርባጃን ፕሬዝዳንት ኢልሃም አሊዬቭ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሀገራቱ በኢነርጂ፣ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ በመከላከያ እና ደህንነት፣ አየር ንብረት ለውጥ መከላከል፣ ስራ እድል ፈጠራና አጠቃላይ በኢኮኖሚ ዘርፍ ትብብራቸውን ማጠናከር የሚቻልባቸውን እድሎች እና አማራጮች መቃኘታቸውን ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ልዑካቸው ያደረጓቸው ጉብኝቶችም የኢኮኖሚ ፋይዳቸው ወሳኝ የሚባል መሆኑን አንስተዋል።
የአዘርባጃን የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች፣ የከተማ ማዘመን፣ አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የተከናወኑ ስራዎች እና የተፈጥሮ ሀብትን ወደ ኢኮኖሚ ጠቀሜታ የመቀየር ተግባራትን የተመለከቱ ጉብኝቶች መደረጋቸውንም ነው የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊዋ ያብራሩት።
ጉብኝቱ ኢትዮጵያ ልምድ የቀሰመችበት መሆኑን ገልጸው የተጀመሩ ስራዎች የበለጠ እንዲጠናከሩ መነሳሳትን መፍጠሩንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በኮሪደር ልማት፣ የቅርሶች ተፈጥሯዊ ይዞታ ተጠብቆ እድሳት ማድረግ፣ የአንድ መሶብ አገልግሎት እና የተለያዩ ስራዎች እያከናወነች እንደምትገኝም አንስተዋል።