ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን በሰው ሰራሽ አስተውሎት ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ ናቸው - ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን በሰው ሰራሽ አስተውሎት ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ጠንካራ ፍላጎት እንዳላቸው የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ በአዘርባጃን ያደረገውን ይፋዊ የስራ ጉብኝት አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ልዑካቸው የአዘርባጃን አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አካዳሚን መጎብኘቱን ገልጸዋል።

አካዳሚው በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ጊዜ ውስጥ የትምህርቱ ዘርፍን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የሰው ሰራሽ አስተውሎት ተደራሽነት በማስፋት ረገድ ውጤታማ ስራ ማከናወኑን ከጉብኝቱ መረዳት መቻሉን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከስድስት ዓመታት በፊት መቋቋሙንና ውጤታማ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በጉብኝቱ ወቅት በምርምር እና ዳታ ልውውጥ ላይ በትብብር ለመስራት በሀገራቱ መካከል መግባባት ላይ መደረሱን ነው የተናገሩት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ልዑካቸው የአዘርባጃን የሕዝብ አገልግሎት እና ማኅበራዊ ፈጠራ የመንግሥት ኤጀንሲ(ASAN) የፈጠራ ማዕከልን ጎብኝቷል።

አሳን የሚሰጠው አገልግሎት ከአንድ መሶብ አገልግሎት ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ በተለይም አገልግሎት አሰጣጡ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዘ መሆኑ ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ያለውን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በሰው ሰራሽ አስተውሎት እንዲታገዝና ጥራቱ እንዲያድግ በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በውይይታቸው በሰው ሰራሽ አስተውሎትና ዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ በትብብር ለመስራት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ጠቁመዋል።

ሀገራቱ በዘርፉ ልምድ ለመለዋወጥ ፍላጎት እንዳላቸውም ነው የተናገሩት።

አጠቃላይ ጉብኝቱ ኢትዮጵያ በቅርቡ ወደ ትግበራ ለገባው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ እና ለዘርፉ ስራዎች አጋዥ አቅም እንደሚሆን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም