በአማራ ክልል ህገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን ለመከላከል የሚደረገው የተቀናጀ ጥረት ውጤት እያስገኘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ህገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን ለመከላከል የሚደረገው የተቀናጀ ጥረት ውጤት እያስገኘ ነው
ባህርዳር፤ የካቲት 21/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ህገ-ወጥ ንግድንና ኮንትሮባንድን በተቀናጀ አግባብ በመከላከል የህግ ተገዥነትን ለማረጋገጥ እየተከናወነ ያለው ስራ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የክልሉ ፍትህ ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ የምርትና ግብይት፣ የገበያ አረጋጊ፣ የፀረ-ኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድ ቁጥጥር ጥምር ግብረ-ኃይል፤ የወንጀል ጉዳዮች ቴክኒክ ኮሚቴ የሥራ አፈጻጸም ግምገማውን ዛሬ በባህርዳር ከተማ አካሂዷል።
በቢሮው የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክተር ሙሉጌታ አሻግሬ እንደገለጹት፤ የቴክኒክ ኮሚቴው 13 ተቋማትን በማቀፍ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።
በበጀት ዓመቱ ያለፉት ወራት በህገ-ወጥ ተግባር ተሰማርተው በተገኙ 190ሺህ 150 የንግድ ድርጅቶችና ማህበራት ላይ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ የሥራ እገዳና የንግድ ፈቃድ ስረዛ እርምጃዎች ተወስደዋል ብለዋል።
ምርቶችን በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ውስጥ ሲያስገቡና ወደ ውጭ ሲያስወጡ ተይዘው በተገኙ 128 ነጋዴዎች ላይ ደግሞ እስከ 12 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራትና የገንዘብ ቅጣት ተላልፏል ነው ያሉት።
ይህ ውጤት ሊመዘገብ የቻለው በተቋማቱ መካከል ያለውን የመረጃ ልውውጥና የጋራ ቁጥጥር በማጠናከር መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢብራሂም መሀመድ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የክልሉን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ጤናማ ለማድረግ ህገ-ወጥ የኬላ ቀረጥ፣ የኮንትሮባንድ ዝውውርና የነዳጅ ስርጭት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት ብቻ 34 ሰዎች ነዳጅን ከማደያ አውጥተው በህገ-ወጥ መንገድ ሲያጓጉዙ እጅ ከፈንጅ መያዛቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የልዩ ልዩ ወንጀሎች መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ደጀን ወዳጅ፤ የነዳጅ፣ የጦር መሳሪያ፣ የመድኃኒትና የምግብ ነክ ምርቶች ህገ-ወጥ ዝውውርን ለማስቆም የተከናወነው ስራ አበረታች መሆኑንና በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።