በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኙ እምቅ ሃብቶችን በሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር በማገዝ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ መስራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኙ እምቅ ሃብቶችን በሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር በማገዝ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ መስራት ይገባል
ዲመካ፤ የካቲት 21/2018(ኢዜአ)፡- በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኙ እምቅ ሃብቶችን በሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር በማገዝ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ መስራት እንደሚገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እና የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አገኘሁ ተሻገር፤ በደቡብ ኦሞ ዞን ዲመካ ከተማ በጂንካ ዩኒቨርሲቲ ለሚገነባው የአርብቶ እና ከፊል አርብቶ አደር የምርምር ኢንስቲትዩት የመሰረተ ድንጋይ አኑረዋል።
ዩኒቨርሲቲው የማዕከሉን ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ የምርምር ስራውን መጀመር ይጠበቅበታል ያሉት አፈ ጉባኤው ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በመጠቀም በየአካባቢው ያሉ እምቅ ሀብቶችን በሳይንሳዊ ምርምር በማስደገፍ የላቀ ጥቅም እንዲሰጡ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የምርምር ማዕከሉ የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ብቻ የሚጠቀሙበት ሳይሆን በሀገር ውስጥ እና በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ ተመራማሪዎች የሚሳተፉበትና ልምድ የሚለዋወጡበት እንደሚሆን ገልጸዋል።
የምርምር ማዕከሉ በተያዘለት ጊዜ በጥራትና በፍጥነት ተጠናቆ ለሚፈለገው ዓላማ እንዲውል አስፈላጊው እገዛ ድጋፍና ክትትል የሚደረግ ይሆናል ብለዋል።
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዮሐንስ ይትባረክ (ዶ/ር)፤ የሚገነባው የምርምር ማእከል በዋነኝነት አራት መሰረታዊ ተልዕኮዎችን ለመፈፀም የሚያስችል ይሆናል ሲሉ አስረድተዋል።
በአካባቢው የግብርና ሥራ እና የእንስሳት ሀብት በሳይንሳዊ የጥናትና ምርምር በማሳደግ የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ማሳደግ አንዱ ሲሆን የቱሪዝም ሀብትን በምርምር በማገዝ ዓለም አቀፋዊ እውቅና እንዲያገኝ ማድረግም ሌላው መሆኑን አንስተዋል።
በአካባቢው ያሉ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን የመሰነድ፣ የማስተዋወቅ እና የማሳደግ ተልእኮን ለማሳካትም ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።