የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም በመላ ሀገሪቱ የአደባባይ ኢፍጣር መርሃ-ግብር ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም በመላ ሀገሪቱ የአደባባይ ኢፍጣር መርሃ-ግብር ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2018(ኢዜአ)፦ የ1447ኛው የረመዳን ፆም ወርን ምክንያት በማድረግ የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም በመላ ሀገሪቱ የሚካሄድ ታላቅ የአደባባይ ኢፍጣር መርሃ-ግብር ማዘጋጀቱን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ።
ምክር ቤቱ መርሃ-ግብሩን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ እንዳመለከተው፣ የዘንድሮው የኢፍጣር መርሃግብር "ነጃሺ ለሀገር" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እና በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በተመሳሳይ ቀን የሚከናወን ይሆናል።
የጠቅላይ ምክር ቤት የፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት ኃላፊ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በመግለጫው ወቅት እንደተናገሩት፤ ረመዳን የአብሮነት፣ የከፍታ እና የጋራ እሴቶቻችን የሚጠናከሩበት ወር ነው።
በመሆኑም የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም በመላ ሀገሪቱ የአደባባይ ኢፍጣር መርሃ-ግብር እንደሚካሄድ ገልጸው፤ መርሃ-ግብሩ የመተሳሰብ እና የመረዳዳት እሴቶችን የሚያጎለብት ነው ብለዋል።
በተጨማሪም መርሃ-ግብሩ ለሀገሪቱ የከፍታ ጉዞ የሚጠበቅብንን አስተዋጽኦ ለማበርከት ቃላችንን የምናድስበት ነው ብለዋል።
ይህንን መርሃ-ግብር በበላይነት የሚያስተባብረው በጠቅላይ ምክር ቤቱ ስር የሚገኘው የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል መሆኑን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል ፕሬዝዳንት ኡስታዝ ሀይደር ከድር በበኩላቸው፣ የዘንድሮው ኢፍጣር በዓይነቱ ለየት ያለና በአንድ ቀን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚካሄድ መሆኑን ገልጸው፤ ወጣቶች ለአንድነት፣ ለልማትና ለእድገት ያላቸውን ሚና የሚያጠናክሩበት መድረክ እንደሚሆንም አክለዋል።
የጠቅላይ ምክር ቤቱ የዑለማ ጉባኤ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሼህ ዓሊ መሐመድ ኤባ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በእለቱ አቅም የሌላቸውን ወገኖች ማገዝ እና መደገፍ በፈጣሪ ዘንድ እጅግ የሚወደድ ተግባር በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
መርሃ-ግብሩ በዋናነት ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶችን ከመፈጸም ባለፈ፣ ለሀገራዊ አንድነትና ለዘላቂ ሰላም በጋራ ፀሎት የሚደረግበት ታላቅ መድረክ እንደሚሆን ገልፀዋል።