ቀጥታ፡

በክልሉ በግብርና ልማት ሥራዎች የታየው እድገትና ማንሰራራት ቀጣይነት እንዲኖረው የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው

አዳማ ፤የካቲት 21/2018(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል በግብርና ልማት ሥራዎች የታየው እድገትና ማንሰራራት ቀጣይነት እንዲኖረው የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

ከሁለት ሺህ በላይ በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ዘርፍ አመራሮች እና ባለሙያዎች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ በአዳማ ገልመ አባገዳ ተካሄዷል።


 

የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ እንደገለፁት በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ሌሎች የግብርና ልማት ሥራዎች የታየው እድገትና ማንሰራራት ቀጣይነት እንዲኖረው ጥረት እየተደረገ ነው።

ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሥራዎች ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሻገርና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በተለይም በኢኒሼቲቭ እየተተገበሩ የሚገኙ የግብርና ልማት ስራዎች በስኬታማነት እንዲቀጥሉ የተጀመሩ ስራዎች ይጠናከራሉ ብለዋል።

በክልሉ  በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በሩዝ፣ በቡናና በሻይ ቅጠል ልማት፣ በአቮካዶ፣ ሙዝ፣ ወተትና ዓሣ ሀብትን ጨምሮ በእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ተጨባጭ ውጤት መምጣቱን ተናግረዋል።

በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ከ3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት መሸፈኑን ጠቅሰው ዕቅዱ እንዲሳካ በማድረግ ረገድ በየደረጃው ያሉ ሙያተኞችና አመራሮች ሚናቸው የጎላ እንደሆነ ገልጸዋል።

በክልሉ መጪው የበልግ እና የ2018/19 የመኸር አዝመራን ለማሳካት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ከወዲሁ እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

ያለን ዕውቀት፣ ክህሎትና ልምድ በማቀናጀት  የተሻለ ምርት ለማግኘት ጠንካራ ሥራ እንደሚሰራ ገልጸው በዘንድሮ የበልግ አዝመራ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማልማት 46 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን አንስተዋል።

ለ2018/19 የምርት ዘመን በመኸር እርሻ 11 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዋና ዋና ሰብሎች ለመሸፈንና 372 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ጠቅሰዋል።

እንደ አቶ ጌቱ ገለጻ በክልሉ በበልግና በመኸር ከሚለማው መሬት ውስጥ 9 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው መሬት በኩታ ገጠም የሚለማ ነው።


 

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በመጪው በልግና በመኸር እርሻ በተለይ ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ላይ ማተኮር ይገባል ብለዋል።

በተጨማሪም የግብርናው ዘርፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን እንዲቋቋም እርሻን ከተፈጥሮ ዝናብ ጥገኝነት ማላቀቅ የሚያስችል ስራን ማስፋት እንደሚገባም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ንጉሴ ደቻሣ (ፕሮፌሰር) እንደገለፁት የምርምርና የቴክኖሎጂ ውጤቶቻችን የአርሶ አደሩ ህይወት መለወጥ የሚችሉ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።


 

የምርምር ውጤቶች አርሶ አደሩ ዘንድ ደርሰው ህይወቱ እንዲለወጥ ለማስቻል የተቀናጀ የባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ ገልጸው ለዚህም ኢንስቲትዩቱ በምርምር የሚያወጣቸውን ቴክኖሎጂዎች ተደራሽ ያደርጋል ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም