ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም መከበር ለልማትና ከድህነት የመውጣት ጥረት ስኬት በተደመረ አቅም መስራት ይገባል

ሀዋሳ፤ የካቲት 21/2018 (ኢዜአ):-ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም መከበር ለልማትና ከድህነት የመውጣት ጥረት ስኬት በተደመረ አቅም መስራት እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ።

ብሔራዊ ጥቅም በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ሕዝብና መንግሥት የሀገሪቱን ደኅንነት፣ ሉዓላዊነት፣ የኢኮኖሚ ዕድገትና ማኅበራዊ ደኅንነት ለማስጠበቅ  የሚሠሩባቸው መሠረታዊ ግቦች መሆናቸው ይታወቃል።

በተለይም የሀገርን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ከማንኛውም ጥቃት መከላከል፤ የሕዝብን የኑሮ ደረጃ የሚያሻሽሉ የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የሀብት ልማት ሥራዎችን ማስፋፋት የግድ ይላል። 

የዜጎችን ክብር፣ ሰላምና ደኅንነት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የማረጋገጥ ጉዳይ የብሔራዊ ጥቅምና የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መርህ ተደርጎ እየተሰራበት መሆኑም ይታወቃል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ኢትዮጵያ የምትገኝበት የምስራቅ አፍሪካ ቀንድና የቀይ ባህር ቀጣና የብዙ ኃይሎች ፍላጎት ያለበት መሆኑን ይገልፃሉ።

በመሆኑም ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም መከበር ለልማትና ከድህነት የመውጣት ጥረት ስኬት በተደመረ አቅም መስራት እንደሚገባ ያስረዳሉ።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ታፈሰ ማቴዎስ (ዶ/ር)፤ ተለዋዋጭና ኢ-ተገማች በሆነው ዓለም ዓቀፋዊ ሁኔታ ውስጥ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅምን ማስከበር የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያነሳችው የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሆኑን የጠቀሱት ምሁሩ ጥያቄው ምላሽ ማግኘት እንዲችል በጋራ መቆም ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።

ባለፉት ዘመናትም ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር እንድትርቅ የተደረገው በታሪካዊ ጠላቶች ሴራ ብቻ ሳይሆን ለብሔራዊ ጥቅም መከበር በጋራ አለመቆማችን በመሆኑ በቀጣይ የባህር በር ባለቤትነትን ጨምሮ ሌሎች ብሔራዊ ጥቅሞችን ለማስከብር መተባበር አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

ሌላው በዩኒቨርሲቲው የጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት መምህርና ተመራማሪ የሆኑት  ምስራቅ ታምሬ (ዶ/ር) የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የፖለቲካ ልዩነት ሳይገድበን በአንድነት መቆም ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲጠናቀቅ መላው ኢትዮጵያዊ ያሳየውን ቁርጠኝነት የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄን ለመመለስም መድገም አለበት ብለዋል።

በተመሳሳይ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ እንዳልካቸው ጀንበሬ (ዶ/ር)፤ ብሔራዊ ጥቅም ከሀገር ህልውና ጋር የተያያዘ በመሆኑ ሁሉም በጋራ መቆም እንዳለበት መክረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም