ቀጥታ፡

ማዕከሉ የጥቁር ህዝቦችን ክብር፣ ባህልና ቅርስ ለማስጠበቅ የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2018(ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፉ የጥቁር ህዝቦች ማዕከል የጥቁር ህዝቦችን ክብር፣ ባህልና ቅርስ ለማስጠበቅ  የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ አስገነዘቡ።  

ዓለም አቀፉ የጥቁር ህዝቦች ማዕከል ዓመታዊ የምክር ቤት ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል።  


 

በጉባዔው ላይ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች፣ ምሁራንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።  

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴን ጨምሮ ለጥቁር ህዝቦች ትግል ፋና ወጊ ሚና ስትጫወት ቆይታለች።  

የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ትግል እርሾ የሆነው የዓድዋ ድል ለዚህ ተጠቃሽ ነው ብለዋል።  

ዓለም አቀፉ የጥቁር ህዝቦች ማዕከል መቀመጫው ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑ ለጥቁር ህዝቦች መብት ትግል ያላትን ቁርጠኝነት ያመላከተ መሆኑን ተናግረዋል።  


 

ማዕከሉ የጥቁር ህዝቦች ክብር፣ ቅርሶችንና ባህል ለማስጠበቅ የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አመልክተዋል። 

ማዕከሉ አፍሪካውያንና በመላው ዓለም የሚገኙ የጥቁር ዝርያ ያላቸው ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ስራዎቻቸውና አሻራዎቻቸው ታትመውና ተሰንደው የሚቀመጡበት የጥናትና ምርምር እንዲሁም የህትመት ማዕከል ሊኖረው እንደሚገባም ጠቁመዋል።  

አሁን ላለው እና ለመጪው ትውልድ እሴቶችና የተለያዩ እውቀቶችን ማሸጋገር ላይ ማዕከሉ ተግቶ ሊሰራ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። 

የኢትዮጵያ መንግሥትም ማዕከሉ የተቋቋመለትን ዓላማ እንዲያሳካ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።


 

የዓለም አቀፉ የጥቁር ህዝቦች ማዕከል ጀነራል ካውንስል ፕሬዝዳንትና የቀድሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ የማዕከሉን ዓላማ ለማሳካት ከተቋማትና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል።

የጥቁር ህዝቦች ታሪክ በማጉላት የተደበቁና በዓለም ደረጃ ጎልተው ሊነገሩ የሚገባቸው ትርክቶችን ጥናት ላይ ተመስርቶ ማውጣት ዙሪያ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።

ተተኪው ትውልድ በቅድመ አያቶች ታሪክ መነሻነት የራሱን ታሪክ የሚጽፍበትን ዕድልና ሁኔታ ለማመቻቸት እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።


 

የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ ለዜጎች ክብር መጠበቅ፣ ለቅርስና ትውልዱ ዕሴት ማሸጋገር ላይ የጀመራቸው ስራዎች እንዲሳኩ ሚኒስቴሩ ተባብሮ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ለዚህም ሚኒስቴሩ ከማዕከሉ ጋር በጋራ ለመሥራት ሥምምነት ላይ መድረሱን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም