ቀጥታ፡

በአባቶቻችን ሉዓላዊነቷ የጸናች ኢትዮጵያን ዳር ድንበር አስከብረን ለማስቀጠል የድርሻችንን እንወጣለን

ደሴ፤ የካቲት 21/2018 (ኢዜአ)፡- በአባቶቻችን ደምና አጥንት ሉዓላዊነቷ የጸናች ኢትዮጵያን ዳር ድንበር አስከብረን ለማስቀጠል የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ የደሴ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።

130ኛው የዓድዋ ድል በዓልን አስመልክቶ "ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ ተስፋ" በሚል መሪ ሀሳብ በደሴ ከተማ ከወጣቶች ጋር የምክክር መድረክ ተካሂዷል።


 

የምክክሩ ተሳታፊ ወጣቶች ሀገራችን ኢትዮጵያ በአባቶቻችን ደምና አጥንት ሉዓላዊነቷ ጸንቶ መቆየቱን አንስተዋል።

ይህን አስከብረን ማቆየት የእኛ ድርሻ በመሆኑ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

ከወጣቶቹ መካከል ወጣት ሰይድ አህመድ እንደገለጸው፣ ዓድዋ የመላው ጥቁር ህዝቦች የነጻነት አርማ፣ የአሸናፊነት ምልክትና የአንድነት ውጤት ነው።

አባቶቻችን በውጭ ወራሪ ጠላት ላለመገዛትና ሀገራቸውን ላለማስደፈር አጥንታቸውን ከስክሰው እና ደማቸውን አፍስሰው ያስረከቡንን ሀገር ዳር ድንበር ለማስጠበቅ የድርሻችንን እንወጣለን ብሏል።

ትክክለኛ ታሪኩን በውል ተረድተን አንድነታችንንና ሰላማችንን በመጠበቅ ለሀገራችንም ሆነ ለከተማችን ብልጽግና የራሳችንን አሻራና ታሪክ እንሰራለን ብሏል።

ሌላዋ የመድረኩ ተሳታፊ ወጣት ማህሌት ይመር በበኩሏ፣ ቅድመ አባቶቻችንና እናቶቻችን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር ለማስከበር የከፈሉት መስዋዕትነት ለዛሬ ነጻነት አብቅቶናል ብላለች።

እኛም ከዓድዋ ድል አንድነትን፣ ጀግንነትንና ህበረ ብሄራዊነትን ተምረን በሰላምና በልማት የራሳችንን ድል ለማስመዝገብ እየሰራን እንገኛለን ብላለች።

አንድነቷ፣ ነፃነቷና ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ የተረከብናትን ሀገር እኛም ለቀጣዩ ትውልድ እናስተላልፋለን ብላለች።

ከዓድዋ ድል አንድነትን፣ አሸናፊነትን፣ ቅንጅትንና ብርታትን ተምረን እኛም በዘመናችን የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችንን በጋራ ድል አድርገን ታሪክ እንሰራለን ያለችው ደግሞ ወጣት ሸዊት ቴዎድሮስ ናት።

ከመንግስት ጎን ተሰልፈንም የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችና የወደባችን ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ ነን፣ ለዚህም የዓድዋ ድል አስተምሮናል ብላለች።


 

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፣ ወጣቱ ትውልድ አንድነቱንና ሰላሙን ጠብቆ በዘመኑ የራሱን ድልና ታሪክ ሊያስመዘግብ ይገባል ብለዋል።

ከዓድዋ ድልም አንድነትና መደማመጥን ተምሮ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በጋራ መጠበቅና የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችና ልማቶችን በመደገፍ የብልጽግና ጉዞ ዳር እንዲደርስ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

ዓድዋ የመላው ጥቁር ህዝቦች ድል፣ ነጻነት፣ አሸናፊነትና አንድነት መሆኑን አስታውሰው፣ ዘወትር ሲዘከር የሚኖር የኢትዮጵያዊያን የአንድነት ምስጢርና ውጤት መሆኑንም ተናግረዋል።

በመድረኩ የደሴ ከተማ አመራሮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም