በዓድዋ ድል የተከፈለውን መስዋዕትነት መነሻ በማድረግ በልማት ስራዎች ላይ የነቃ ተሳተፎ እናደርጋለን - ኢዜአ አማርኛ
በዓድዋ ድል የተከፈለውን መስዋዕትነት መነሻ በማድረግ በልማት ስራዎች ላይ የነቃ ተሳተፎ እናደርጋለን
አሶሳ፤ የካቲት 21/2018(ኢዜአ)፦ በዓድዋ ድል የተከፈለውን መስዋዕትነት መነሻ በማድረግ በልማት ስራዎች ላይ የነቃ ተሳተፎ ማድረግ ይጠበቅብናል ሲሉ የአሶሳ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።
130ኛው የዓድዋ ድል በዓል በፓናል ውይይት እና በተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች በአሶሳ ከተማ ተከብሯል።
በወቅቱ ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች እንዳሉት፤ በዓድዋ ድል ጀግኖች ኢትዮጵያውያን የከፈሉት መስዋዕትነት ለአሁኑ ትውልድ ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ ሀገር እንዲያስረክቡ አስችሏቸዋል።
ከወጣቶቹ መካከል አቶም ሀሚድ እንዳለው የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን የውጪ ሀይሎችን በጀግንነት ያሸነፉበት እና ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንድትቀጥል ያደረጉበት ታሪካዊ ድል ነው።
ድሉ ለአሁኑ ትውልድ ጽናትንና አይበገሬነትን ያስተማረ በመሆኑ የተገኘውን ነፃነት በመጠቀም በልማት ስራዎች ላይ የነቃ ተሳትፎ እናደርጋለን ብሏል።
ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወጣት አሪሳላ ከድር እንደገለፀችው፤ በዓድዋ ድል መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖች በወቅቱ የነበራቸውን የሀገር ፍቅር በተግባር ያሳዩበት እና ያለምንም ልዩነት የተሳተፉበት ነበር።
በአሁኑ ወቅት የወጣቶችን ተሳትፎ የሚጠይቁ እና ሀገርን ከፍ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ በመሆኑ ትውልዱ ለዳግማዊ ዓድዋ ድል ራሱን ማዘጋጀት እንዳለበት ገልጻለች።
የወጣቶች ተሳትፎ ለሀገር ልማት እና ዕድገት ወሳኝ በመሆኑ በአሁኑ ሰዓት ወቅቱ የሚጠይቀውን የዲጂታል ዕውቀት በመሰነቅ ተወዳዳሪና ለሀገር ኩራት የሚሆን ወጣት ሆነን መገኘት ይገባናል ነው ያለችው።
የዓድዋ ድል ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለአንድ ዓላማ በተሰባሰቡ ጀግኖች የተገኘ ድል በመሆኑ ለአንድ ዓላማ በጋራ መቆምን ልንማርበት ይገባል ያለው ደግሞ ሌላው የከተማዋ ወጣት አላዛር ተካልኝ ነው።
የአሁኑ ትውልድ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በመረዳት ለሀገር ህልውና የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም ጠቁሟል።