የዓድዋ ድል እና የሕዳሴ ግድብ ስኬት የአፍሪካውያን የመነሳት ዘመን አኩሪ ገድሎች ናቸው - የታሪክ ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ድል እና የሕዳሴ ግድብ ስኬት የአፍሪካውያን የመነሳት ዘመን አኩሪ ገድሎች ናቸው - የታሪክ ምሁራን
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2018(ኢዜአ)፦ የዓድዋ ድል እና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬት የኢትዮጵያውያን ጀግንነት የተገለጠበት የአፍሪካውያን የመነሳት ዘመን አኩሪ ገድሎች መሆናቸውን የታሪክ ምሁራን ገለጹ።
የዓድዋ ድል የታሪክ መዛግብት ከትበው ያልጨረሱት ቅድመ አያቶች በደምና አጥንታቸው ለኢትዮጵያ ሉዓላዊ ነፃነትና ክብር የከፈሉት የዓለም ጥቁር ህዝቦች ድልና የመነሳት ዘመን የታሪክ ማኅተም ነው።
የዓድዋ ጀግኖች ለኢትዮጵያ አንድነትና ክብር በፋሺስት ወራሪ የጣሊያን ኃይል ላይ የተጎናጸፉት አኩሪ የጦር ሜዳ ጀብዱም ለአሁኑ ትውልድ የልማት አርበኝነትን አውርሶ ያለፈ የነፃነት ምልክት ሆኗል።
የአሁኑ ትውልድም በቅድመ አያቶቹ ጀግንነትና በትወልድ ቅብብሎሽ የጸናች ኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚያደርጋቸው የልማት ጥረቶች በሁሉም መስክ አስደማሚ ስኬቶችን አስገኝተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬትም አፍሪካውያን የተፈጥሮ ሃብታቸውን በራስ አቅም አልምተው የመጠቀም መብታቸውን በተግባር ያረጋገጠ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት መሰረት የጣለ የዘመኑ ዳግማዊ ዓድዋ ተደርጎ ተወሰዷል።
ኢትዮጵያውያን በሕዳሴ ግድብ ስኬት የነበራቸው በሕብር የተገመደ ትብብርም የዓድዋ ጀግኖችን ያስታወሰና ሀገርን ከድህነት አረንቋ ወደ ብልጽግና ማማ ለማሸጋገር የተደረገ የልማት አርበኝት መገለጫ ነው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍቅርተ ታምር፤ የዓድዋ ድል የኢትዮጵውያን የሕብር ግማድ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ቀንዲል ነው ብለዋል።
በዚህ ዘመንም ቅድመ አያቶች በዓድዋ ሰንሰለታማ ተራሮች የተጎናጸፉትን አኩሪ የጦር ሜዳ ጀብዱ የአሁኑ ትውልድ በጉባ ተራሮች ግርጌ ታላቁ ሕዳሴ ግድብን እውን በማድረግ ታሪክ መስራቱን ገልጸዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም ጫና ያልበገረው በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ያሳኩት የአንድነት ምሳሌና የጋራ አሻራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የዓድዋ ድል የነፃነት ማኅተም፤ ሕዳሴ ደግሞ የብልጽግና ጉልበት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ዳግማዊ የዓድዋ ድል የጋራ ምልክት ህያው አሻራ ለመሆን መብቃቱን አንስተዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሚያመነጨው ኃይልም ቀጣናዊ የኃይል ትስስርን በማፋጠን በአጭር ጊዜ ውስጥ የአፍሪካን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ እንደሚቻል ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል።
በግንባታ ወቅት የነበረው የኢትዮጵያውያን ትብብርም ግዙፍ ሀገራዊና አህጉራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ማሳካት እንደሚቻል መነቃቃትን በመፍጠር ትምህርት የሰጠ ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።
እውቁ የታሪክ ምሁርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካሪያ እንደሚሉትም፤ በኢትዮጵያ የትውልድ ቅብብሎሽ የነፃነት ታሪክ ውስጥ የዓድዋ ድል ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው የታሪክ አሻራችን ነው።
ቅድመ አያቶች የተጎናጸፉትን የዓድዋ ድል የዓለም መገናኛ ብዙኅን የሚገልጹበት ቃላት እስኪቸግራቸው ድረስ የጥቁር ህዝቦችን ጀግንነት በማድነቅ የፊት ገፆቻቸው ማድመቂያ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የዓድዋ ድልና ታላቁ ሕዳሴ ግድብ የዜጎች ሕብረትና አንድነት የኢትዮጵያን መፃኢ እጣ ፋንታና ተስፋ ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገር እንደሚችል ሕያው ማሳያ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አፍሪካ በአጀንዳ 2063 እውን ለማድረግ ያስቀመጠቻቸውን ግቦች ለማሳካት የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ አስተዋጽኦ የሚያደርግ አህጉራዊ የልማት ፕሮጀክት መሆኑንም አንስተዋል።
ሌላኛው የታሪክ ጸሐፊና የኢትዮ-ዓረብ ተመራማሪ ፕሮፌሰር አደም ካሚል፤ የሕዳሴ ግድብ የዚህ ዘመን ትውልድ የይቻላል መንፈስ ያስገኘው ዳግማዊ የዓድዋ ድል የልማት ስኬት ነው ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና ዓድዋ ልማትና ጀግንነት የተጣመሩባቸው አህጉራዊ ድሎች ናቸው ያሉ ሲሆን፤ የሕዳሴ ግደብም የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን መጎናጸፍ የሚያስችል የልማት ድል መሆኑን ገልጸዋል።