ኢትዮጵያ በባህር በር ጉዳይ ያላትን ሀቅ ለዓለም በማስገንዘብ ኃላፊነታችንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በባህር በር ጉዳይ ያላትን ሀቅ ለዓለም በማስገንዘብ ኃላፊነታችንን እንወጣለን
ወላይታ ሶዶ፣ የካቲት 21/2018 (ኢዜአ):-የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ የኢትዮጵያን ሀቅ ለዓለም በማስገንዘብ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።
የባህር በር ለኢትዮጵያ የብሔራዊ ደህንነትና ሉአላዊነት ጉዳዩ ከመሆኑ ባሻገር የሀገሪቱን የከፍታ ጉዞ እውን ለማድረግ በወሳኝ ጊዜ የተነሳ የህልውና ጥያቄ መሆኑንም ምሁራኑ አንስተዋል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር አሸቱ ተስፋዬ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ከባህር በር ጋር ለዘመናት የተቆራኘ ታሪክ ያላትና የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት ናት።
የባህር በር የውጭ ንግዷን የምታሳልጥበት በመሆኑ ኢትዮጵያን ከውሃ አካል ነጥሎ ማየት እንደማይቻል ገልጸው፣ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠረው ስህተት ከባህር ለዘመናት እንድትነጠልና ጫና እንዲፈጠርባት አድርጓል ብለዋል።
አሁን በአዲስ እየተነሳ ያለው የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ተገቢና ህጋዊ መሰረት ያለው ከመሆኑ ባለፈ ብሔራዊ ጥቅምንና ሉአላዊነትን የማስከበር ጉዳይ በመሆኑ ተገቢ ምላሽ እስኪገኝ ድረስ የኢትዮጵያን ሃቅ ለዓለም ለማስገንዘብ ሙያዊ ግዴታቸውን በአግባቡ እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ መመለስ ለጎረቤት ሀገራትና ለቀጣናው ሀገራት ያለው ፋይዳ የላቀ መሆኑንም ረዳት ፕሮፌሰር አሸቱ አንስተዋል።
በቀጣናው ሀገራት የኢኮኖሚ ትብብርን በማጠናከር የጋራ ተጠቃሚነትና ዕድገት ላይ ጉልህ ሚና እንደሚጫወትም ነው ያስረዱት።
የባህር በር ባለቤት መሆን የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚያረጋግጥ በመሆኑ ከመንግስት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በተጨማሪ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በጋራ ሊተጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ስነ ዜጋ እና ስነ ምግባር ትምህርት ክፍል የሰላምና ደህንነት ትምህርት መምህርና ተመራማሪ ወንድሙ አዴ በበኩላቸው "የባህር በር ጉዳይ ተገቢ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ ሀገር ያላትን እውነት በማሳወቅ ኃላፊነቴን እወጣለሁ ብለዋል።"
የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር የተቆራኘና ህጋዊ መሠረት ያለው መሆኑን ጠቅሰው በሴራ ያጣችውን የባህር በር ለማስመለስ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማገዝ ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል።
ምጽዋም ሆነ አሰብ የኢትዮጵያ ሀብት እንደነበሩ ታሪክ አይሽራቸውም ያሉት መምህርና ተመራማሪው፣ የባህር በር ያጣንበት መንገድ ኢትዮጵያን ከ30 ዓመታት በላይ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏል ብለዋል።
የባህር በር ጥያቄ ኢትዮጵያ የሚገባትን ለማግኘትና ካላት የማደግ ፍላጎት የተነሳ በትክክለኛ ጊዜ የተነሳ የህልውና ጉዳይ እንጂ የቅንጦት እንዳልሆነም አንስተዋል።
በሀገር ጥቅምና ሉአላዊነት ላይ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ትብብርን ማጠናከር እንዳለባቸው አንስተው ኢትዮጵያ ያላትን እውነት ለዓለም በማሳወቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።