ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ ለአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነት የተሰጠው ትኩረት አመርቂ ውጤት አስገኝቷል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ ለአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነት የተሰጠው ትኩረት አመርቂ ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻሉን የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር ዓባይ ገለጹ።

የአዲሰ አበባ ከተማ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የኢትዮጵያ ታምርት ሳምንታዊ የንቅናቄ ኤክስፓ ማጠቃለያ መርሃ ግብር በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የዕውቅና እና ምስጋና መርሃ ግብር አካሂዷል።

"ኢትዮጵያ ታምርት፤ አዲስ አበባ ትበልፅግ" በሚል መሪ ሃሳብ ሲካሄድ በቆየው መርሃ ግብር ላይ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት፣ አምራቾች ኢንዱስትሪዎች የዕውቅና ሰርተፊኬትና ሽልማት ተበርክቷል።


 

በዚሁ ጊዜ አቶ ጃንጥራር ዓባይ፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለከተማዋ አምራች ኢንዱስትሪዎች ውጤታማነት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።

ንቅናቄው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ማነቆዎችን አፋጣኝ መፍትሔ በማስገኘት ቀጣይነት ያለው የምርት ዕድገት እንዲስመዘግቡ እያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም የግብዓት አቅርቦት እጥረትን በመቅረፍ፣ የገበያ ትስስርን በማጠናከርና ለዘርፉ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ አሰራሮችን በመዘርጋት በኩል ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አምራች የኢንዱስትሪዎችን የምርታማነት አቅም በማጎልበት ከፍተኛ አመርቂ ውጤት እንዲመዘገብ እያስቻለ መሆኑን አብራርተዋል።

በቀጣይም የኢንዱስትሪ ምርታማነት አቅምን የበለጠ ለማጎልበት የድጋፍና ክትትል ስራዎችን የማጠናከር ስራዎች ትኩረት እንደሚሰጣቸው ጠቅሰዋል።


 

የአምራቹ ዘርፉ የታለመለትን ግብ ይመታ ዘንድ የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግና አደረጃጀቶችን በመፍጠር በአምራቾች የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ይሰራል ነው ያሉት።

በማጠቃለያ መርሀ ግብሩ የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ አምራቾችና አጋር አካላት እውቅናና ሽልማት የተበረከተ ሲሆን፤ በፕሮግራሙ የአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በአዲስ አበባ 3ሺህ 900 አነስተኛና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች የሚገኙ ሲሆን አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬ ወጪን በማዳን የሀገርን ዕድገት እያፋጠኑ እንደሚገኙ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም