በጉጂ ዞን በሰባት ወራት ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ የቡና ምርት ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በጉጂ ዞን በሰባት ወራት ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ የቡና ምርት ተሰበሰበ
አዶላ ፤ የካቲት 21/2018 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በሰባት ወራት ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ የቡና ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጉጂ ዞን በኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥራት ያለውና በዓለም ገበያ ተፈላጊ የሆነ "ስፔሻሊቲ" ቡና በማምረት በግንባር ቀደምትነት ከሚታወቁ አካባቢዎች መካከል ይጠቀሳል።
በቅርብ ዓመታት በተደረገው የኩታ ገጠም የግብርና ልማት በዞኑ የቡና ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረ ሲሆን አብዛኛው አርሶ አደር የተፈጥሮ ማዳበሪያን ስለሚጠቀምና ምርቱ ኦርጋኒክ ስለሆነ በከፍተኛ ዋጋ ይሸጣል።
በጽህፈት ቤቱ የቡናና ሻይ ልማት ባለሙያ አቶ ብርሀኑ ፈይሳ ለኢዜአ እንዳሉት በበጀት ዓመቱ በዞኑ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ቡና ለማምረት ታቅዶ ሲሰራ ቆይቷል።
እስካሁን በተካሄደው እንቅስቃሴ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል የቡና ምርት መሰብሰብ መቻሉን ጠቅሰው ምርቱ የተሰበሰበው ከ177 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዞኑ የቡና ልማትን ለማስፋፋት ጽህፈት ቤቱ ባለፉት ዓመታት የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ከጅማ፣ ከይርጋለም እና አወዳይ ግብርና ምርምር ማእከል ተቀብሎ ማከፋፈሉንም አስታውሰዋል።
የተሻሻሉት የቡና ዝርያዎች ድርቅና በሽታን በመቋቋምና ፈጥኖ በመድረስ ከፍተኛ ምርት የመስጠት አቅም እንዳላቸው አስረድተዋል።
ከነባሩ የቡና ዝርያ በሄክታር ከ5 እስከ 7 ኩንታል ይገኝ የነበረውን ምርት ከተሻሻለው ዝርያ ወደ 12 ኩንታል ማሳደግ መቻሉን በመጠቆም።
የዞኑ ንግድ የጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አሬሩ ዋሬ፣ ከተሰበሰበው የቡና ምርት ውስጥ ከ75 ሺህ ቶን በላይ ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ቡና ለማእከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ ባለፉት ሰባት ወራት 10 ሺህ ቶን የሚጠጋ ምርት ለማእከላዊ ገበያ መቅረቡን ገልጸዋል።
በዚህም በየአመቱ ከዞኑ የሚሰበሰበው የቡና ምርት በብዛትም ሆነ በጥራት እየተሻሻለና እድገት እያሳየ መምጣቱን አብራርተዋል።
በቡና ንግድ ከተሰማሩት መካከል የአዶላ ከተማ ነዋሪ አቶ ጌታቸው ጎልጃ፣ ለቡና ልማት የተሰጠው ትኩረት አምራቹንና ባለሀብቶችን ተጠቃሚ አድርጓል ብለዋል።
በዞኑ የተቋቋመው የቡና ጥራትና ጣዕም የቅምሻ ማዕከል ለአርሶ አደሩንም ሆነ ለባለሀብቱ የስራ መነሳሳት መፍጠሩን እንዲሁ።
በዚህ ረገድ በተያዘው አመት ጥራትና ብዛት ያለው ምርት ከአርሶ አደሩ በመሰብሰብ ለገበያ ለማቅረብ እየሰሩ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በዞኑ አዶላ ዙሪያ ወረዳ የአንፈራራ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ገመዳ ሀላኬ፤ በቡና ልማት የበርካታ አመታት ልምድና ተሞክሮ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች ድርቅና በሽታ በመቋቋም ከፍተኛ ምርት በመስጠት ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።
ነባሩን የቡና ተክል ከማሳቸው ላይ በማንሳት በየአመቱ የተሻሸሉ የቡና ችግኝ በመትከል ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።