ቀጥታ፡

ከስብራት ወደ ማንሰራራት የተሻገረው የአማራ ክልል ቱሪዝም

የለውጡ መንግስት ትኩረት ከሰጣቸው አምስት የኢኮኖሚ ምሰሶዎች መካከል አንዱ የሆነው የቱሪዝም ዘርፍ በአማራ ክልል እመርታዊ ለውጥ እያስመዘገበ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ከጭስ አልባው ኢንዱስትሪ ለዓመታት የሚገባትን ያህል ጥቅም ሳታገኝ ብትቆይም የለውጡ መንግስት በአዲስ እይታ ለመዳረሻ ልማቶች በሰጠው ትረኩረት በዘርፉ መነቃቃት ተፈጥሯል።

በአማራ ክልል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በገበታ ለሀገርና በገበታ ለትውልድ የለሙ የቱሪዝም መዳረሻዎች ክልሉ ያለውን ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶች የበለጠ የሚያሳድጉ ናቸው።


 

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ መልካሙ ጸጋዬ፣ ክልሉ በርካታ የቱሪዝም ሀብቶች ቢኖሩትም ሀብቱን ለይቶ፣ አልምቶና ጠብቆ ከመጠቀም አኳያ ውስንነቶች ነበሩ።

የለውጡ መንግስት የተከተለው የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ አተያይ ለቱሪዝም ዘርፉ አዲስ ብስራት ይዞ መምጣቱን ገልጸዋል።

በዚህም በክልሉ ተረስተውና ለጉዳት ተጋልጠው የነበሩ ቅርሶች ጥገና እንደተደረገላቸውና አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች መልማታቸውን አመላክተዋል።

ለአብነትም በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ተገንብቶ በቅርቡ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት በቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ አዲስ መነቃቃት መፍጠሩን አንስተዋል።


 

የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርትም የጣና ገዳማትን ለመጎብኘት የሚመጡ እንግዶች ምቹና አይረሴ ጊዜ ማሳለፍ እንዲችሉ መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል ብለዋል።

በክልሉ ውጤታማ የቅርስ ጥገና፣ ጥበቃና እንክብካቤ ሥራዎች መሰራታቸውንም አቶ መልካሙ ገልጸዋል።

በለውጡ መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ የተሰጠው ትኩረት የክልሉን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ከስብራት ወደ ማንሰራራት ማሻገሩንም ተናግረዋል።

በክልሉ በመንግስትና በሕብረተሰቡ ትብብር የ49 ቅርሶች ጥገና እየተከናወነ እንደሚገኝም ጨምረው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም