የዓድዋ ድል የጋራ መግባባትና የአንድነት ምልክታችን ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ድል የጋራ መግባባትና የአንድነት ምልክታችን ነው
ወልዲያ፤ የካቲት 21/2018 (ኢዜአ)፡-የዓድዋ ድል የጋራ መግባባትና የአንድነት ምልክታችን ነው ሲሉ የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህር መብሬ ታዴ ለኢዜአ እንደገለጹት አያት ቅድመ አያቶቻችን በዓድዋ ያስመዘገቡት ድል አኩሪ ታሪክ ነው።
ይህም ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን መላው ጥቁር ህዝብ አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲሄድ ያስቻለ በመሆኑ ለዘለአለም ሲዘከር የሚኖር መሆኑን ገልጸዋል።
የዓድዋ ድል ትልቁ ምስጢር መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት ተሰልፈው በመፋለም ያስመዘገቡት ድል በመሆኑ ለእኛ ታላቅ ኩራትና ትምህርት የምንቀስምበት ነው ብለዋል።
አባቶቻችን ለውጭ ወራሪ አሳልፈን አንሰጥም በማለት አስጠብቀው ያቆዩትን አገር የአሁኑ ትውልድም ችግሮችን በውይይትና በንግግር በመፍታት ለብሄራዊ ጥቅም በጋራ ሊቆም እንደሚገባ መክረዋል።
የዓድዋ ዘመቻ መሪንና የመሪን ቃል ያከበረ ህዝባዊ ጨዋነት የተገለጠበት በመሆኑ የአሁኑ ትውልድም ከመሪው ጋር በመተጋገዝ ሀገሩን ማሳደግ እንዳለበት ያስተማረ መሆኑን አስረድተዋል።
ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ለመመከት በጋራ በመሰለፍ ትግል የምናደርግበት ወቅት ላይ የምንገኝ በመሆኑም ትውልዱ ጸንቶ የሀገሩን ክብር ሊያስጠብቅ ይገባል ብለዋል።
"እየተገነቡ ያሉት ሜጋ ፕሮጀክቶች እንደ ዓድዋ ድል ሁሉ የአፍሪካ ተምሳሌት ናቸው" ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር ኑሩ አህመድ(ዶ/ር) ናቸው።
የዘንድሮውን የዓድዋ ድል የምናከብረው ድህነትን ለማስወገድ በሚደረገው ትግል የተገኙ ለውጦችን ይበልጥ አጠናክረን በማስቀጠል ነው ብለዋል።
ወጣቱ ትውልድ በእውቀቱ፣ በጉልበቱና በገንዘቡ ርብርብ ማድረግ እንዳለበት ጠቁመው እኛ ምሁራንም ችግር ፈች ምርምሮችን በማድረግ ውጤታማ ስራ ለመስራት እንተጋለን ብለዋል።
ተግዳሮቶችን ለማለፍ የውስጥ አንድነትን በማስጠበቅና የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ይበልጥ በማጠናከር መስራት እንደሚገባም አስረድተዋል።
አክለውም ኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤት የማድረግ ጥያቄ ዳር እንዲደርስ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ የበኩላችንን ድርሻ ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
በሀገራችን አሁን ላይ እያጋጠሙ ያሉ ወቅታዊና ውስጣዊ ፈተናዎችን ለማለፍ ከዓድዋ ዘመቻና ድል በመማር በቁርጠኝነት ልንሰራ ይገባል ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።