ቀጥታ፡

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ለጀመረችው የብልጽግና ጉዞ መሠረት የሚጥል ነው - ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን

አሶሳ፤ የካቲት 21/2018(ኢዜአ)፦ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ለጀመረችው የብልጽግና ጉዞ መሠረት የሚጥል መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ።

130ኛው የዓድዋ ድል በዓል በአሶሳ ከተማ በፓናል ውይይት እና በተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ተከብሯል።

ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የዓድዋ ድል የአሰባሳቢ ትርክትን አስፈላጊነት ያስመሰከረ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ቅኝ ገዢዎችን በተባበረ ክንድ ድል ያደረጉበት ነው።

ድሉ ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ ለጀመረችው ሁለንተናዊ ብልጽግና መረጋገጥ መሠረት የሚጥል እና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በጽኑ መሠረት ላይ ለመጣል የሚያግዝ እንደሆነ ገልጸዋል።


 

ኢትዮጵያውያን በትብብር ያሳካናቸው ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የዳግማዊ ዓድዋ ማሳያዎች መሆናቸውን ጠቁመው የኢትዮጵያን ከፍታ በዓለም መድረክ ለማሳየት ሁላችንም በአንድነት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ህዝቦች ድል በመሆኑ ድሉ በጭቆና ውስጥ ለነበሩ ሌሎች ሀገራት የነፃነት ንቅናቄ መነሻ በመሆን ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበረውም አስታውሰዋል።

በመድረኩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የፀጥታ አካላት እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም